በክልሉ የዶሮ ርባታ ልማት እንዲስፋፋ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

Spread the love

በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ የሚዲያ ቡድን አባላት በዶሮ ልማት ያሉ ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ወጣት ኑርሰላም ሀሰን እና ወጣት መሃመድ ካሳ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵ ህዝቦች ክልል በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ አስተዳደር በዶሮ ርባታ ስራ ከተደራጁ ማህበራት መካከል ናቸው።

3 ሆነው በመደራጀት ከጀመሩትን የአንድ ቀን ጫጩት ስራ ወደ እንቁላል ጣይ ዶሮ በመሸጋገር ውጤታማ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በውዴታ ዶሮ እርባታ ማዕከል በ200 መቶ እንቁላል ጣይ ዶሮ የተጀመረውን ስራ አስፍተው አሁን ላይ 1000 ዕንቁላል ጣይ ዶሮዎች በማርባት በቀን እስከ 500 እንቁላል እያቀረቡ መሆኑን ይናገራሉ ፡፡

ከመንግስት የውሃ ፣የመብራትና የእርባታ ቦታ መመቻቸቱ እና የባለሙያ ድጋፍ እና ክትትል ለስራቸው ውጤታማነት አይነተኛ ሚና እንደነበረውም መስክረዋል፡፡

ያገኙትን የእንቁላል ምርት ከራስ ፍጆታ በዘለለ የአካባቢውን የእንቁላል ዋጋ ንረት ለማርገብ ከአካባቢው የእንቁላል ዋጋ በዝቅተኛ ዋጋ እያቀረቡ እንደሚገኙም አስረድተዋል ፡፡

በምግብ ማቀነባበር ስራ የተሰማሩ ወጣት መቅደስ እንዳለ እና ወጣት ረድኤት ሰለሞን የእንቁላል ምርትን በአካባቢው ከተደራጁ ማህበራት በብዛት እና በቅናሽ ዋጋ በመግዛት ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ መስክረዋል፡፡

የቴፒ ከተማ አስተዳደር ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽ/ቤት የእንስሳት ዘርፍ ባለሙያ አቶ አሸናፊ ማርዬ በከተማው የዶሮ ርባታ ልማት ስራ ከአንድ መቶ በላይ ወጣቶች ተደራጅተዋል።

ወጣቶቹን አስፈላጊውን ድጋፍ በማመቻቸት ዉጤታማ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎች ተጠናክሮ እየተከናወኑ እንደሚገኝም አቶ አሸናፊ ተናግረዋል ፡፡

የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ በረከት ኢዮብ ለሚዲያ ቡድኑ በሰጡት ማብራሪያ እንደ ክልል የተትረፈረፈ ሌማት እንዲኖር ከሚሰሩ ስራዎች መካከል የዶሮ ርባታ ልማት አንዱ መሆን ጠቅሰዋል።

ለዘርፉ ስራ ወጤታማነት መረጋገጥ በሼድ ግንባታ፣ በአንድ ቀን ጫጬት አቅርቦትና በህክምና ስራዎች በተደረገው ድጋፍ ተጨባጭ ለውጥ እየተገኘ መሆኑንም ገልጸዋል ።

የዶሮ ርባታ ልማት ስራ ከቤት ውስጥ የገበታ ፍጆታ አቅርቦት ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች እና ለሌሎች የክልሉ ነዋሪዎች የስራ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝም ወ/ሮ በረከት አብራርተዋል ፡፡

በክልሉ ባለፉት ሶስት አመታት የዶሮ ርባታ ልማት እንዲስፋፋ ትኩረት ተሰጥቶ በተሰራው ስራ 718 የዶሮ መንደሮች መፈጠራቸውን የገለፁት ኃላፊዋ በመኖ አቅርቦት የሚታየውን ማነቆ በዘላቂነት ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *