ቲካሻ ቤንጊ የሸኮ ብሔር የአዲስ ዘመን ብስራት ፣ የምስጋናና ቱባ የአብሮነትና ባህላዊ ክዋኔዎችን የያዘ ነው ፦ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ

Spread the love

2ኛው የሸኮ ብሔር የዘመን መለወጫና የምስጋና በዓል “ቲካሻ ቤንጊ” የፓናል ውይይት በሸኮ ወረዳ እየተከበረ ነው።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤና የሸኮና አካባቢው ምሁራን የጥናትና ምርምር ማህበር የበላይ ጠባቂ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ የፓናል መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት ቲካሻ ቤንጊ የሸኮ ብሔር ለዘመናት ጠብቆ ያቆየው ስለ ዘመን አቆጣጠር ፣ ለታላላቆች ያለውን ክብርና አብሮነት ፣ ቱባ ባህላዊ እሴትና ክዋኔዎችን የያዘ ሀብት ነው ብለዋል።

ቲካሻ ቤንጊ የሸኮ ብሔር የአዲስ ዘመን ብስራት ፣ በጋራ ለፈጣሪያቸው ምስጋና የሚያቀርቡበት ፣ የቀደምትነትና የእውቀት ባለቤት መሆናችን ማሳያና አንዱ መገለጫ ነው ብለዋል። ቲካሻ ቤንጊ ለዘመናት ተቋርጦ ከነበረበት አምና ለመጀመሪያ ጊዜ በድምቀት መከበር መጀመሩን ገልጸው ዘንድሮ ለትውልድ መተላለፍ በሚችል መልኩ በአዲስ አበባ ፣ በ3 ወረዳዎችና በ3 ከተማ አስተዳደሮች ከቀበሌ ጀምሮ በድምቀት መከበሩን ጠቁመዋል።

አቶ ወንድሙ አክለውም ለቲካሻ ቤንጊ መጀመር የሸኮና አካባቢው ምሁራን የጥናትና ምርምር ማህበር ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸው ምሁራን የህዝባቸውን ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥና አብዝቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የሸኮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሪ ጉርሙ ቲካሻ ቤንጊ ላለፉት 50 እና ከዚያ በላይ አመታት ሳይከበር ተቆርጦ የቆየና አምና ለመጀመሪያ ጊዜ መከበር የጀመረ የሸኮ ብሔር የአዲስ ዘመን ጅማሬ ፣ የራሱ ጥንታዊ የዘመን መቁጠሪያ ካላንደርና ማህበራዊ ፍልስፍናውን የሚያሳይ በዓል ነው ብለዋል።

ቲካሻ ቤንጊና ወርሀ ጥር ልዩ ትስስርና ትርጓሜ ያለው መሆኑን የገለጹት አቶ አሪ ንጉስ ኮይናብን መሰረት አድርጎ ዘመኑን መቁጠር የጀመረበትና በየዘመኑ ፈጣሪውን በጋራ እያመሰገነ የመጣበት የታሪክ ሂደትና ዑደትን የሚያሳይ ነው ብለዋል። ወርሀ ጥር ከክረምቱ ዝናብና ጎርፍ ፣ ከአውሬና ፅልመት አልፈው ወደ ጥጋብና የምርት ዘመን ላሸጋገራቸው ፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት በዓል ነው ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁር በሆኑት በዕጩ ዶክተር አማረ ፈንታው ቲካሻ ቤንጊና የሸኮ ህዝብን የተመለከ ጥናታዊ ሰነድ እየቀረበ ይገኛል።

በፓናል ውይይት መድረኩ የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የተከበሩ ዘሙ ተስፋዬ ፣ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታን ጨምሮ የዞንና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፣ በተለያዩ አካቢዎች የሚኖሩ የብሔሩ ተወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ መሆናቸዉን የቤንች ሸኮ ዞን ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *