




ዛሬ የጎበኘነው ልማት የሚያሳየው የተገለጠ ዓይን እና የጠራ ሃሳብ ሲኖር በአጠረ ጊዜ ውስጥ ሀገር መቀየር የሚያስችል ዕድል መኖሩን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዳውሮ ዞን የተገነባውን የኢቲ ማዕድን ልማት አ.ማ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት፥ እንዲህ ያለው ዕድል ተግቶ የማየት እና የመስራት ልምምድ ሲጨመርበት ደግሞ በአጭር ጊዜ ከድህነት ለመውጣ እንድንችል ያደርገናል ብለዋል።
ከለውጡ በኋላ ኢኮኖሚው ብዝኃ ዘርፍ እንዲሆን በማድረግ አዲስ የእይታ መስክ ተፈጥሮ ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
ይህን ተከትሎ ከዚህ በፊት በቱሪዝም እና በማዕድን ልማት እምብዛም የማይታወቀው ዳውሮ ዞን ቀደም ሲል በሀላላ ኬላ የቱሪስት መዳረሻ የጀመረው የአካባቢው ለውጥ አሁን ደግሞ በማዕድን ልማት ቀጥሎ የአካባቢው እምቅ አቅም እየወጣ መሆኑን ጠቁመዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
