



ከጎሬ-ማሻ-ቴፒ አስፓልት መንገድ ስራ ፕሮጀክት ጋር የአስፓልት መንገድ ግንባታ ስራውን ከከተሞች በፍጥነት ለመጀመር ያለመ ውይይት በማሻ ከተማ ተካሂዷል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በወቅቱ እንደተናገሩት የአስፓልት መንገድ ግንባታ ስራው በፍጥነት እንዲጀመር የከተማ አስተዳደር መዋቅሮች እና በከተሞች ዙሪያ የሚገኙ ወረዳዎች ንብረት የማስነሳትና ከካሳ ክፊያ ጋር ተያይዞ ያለውን ጉዳይ ከህብረተሰቡ በመወያየት መግባባት ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የአስፓልት መንገድ ስራው ከከተማ መጀመሩ ለከተሞች እድገት ዘርፌ ብዙ ጠቀሜታ አለው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ስራውን በፍጥነት ለማስጀመር የዞኑ አስተዳደር ከከተማና ወረዳ አስተዳደር መዋቅሮች ጋር በመሆን በልዩ ትኩረት ይሠራል ሲሉም ገልፀዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ከንቲባዎችና የወረዳ አስተዳዳሪዎች በወቅቱ እንደገለፁት ከንብረት ማስነሳትና ካሳ ክፊያ እንዲሁም ግመታ ጋር ተያይዞ ያለውን ጉዳይ በፍጥነት ለመጨረስ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
መንገዱ በሚያልፍባቸው አካባቢ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋርም ውይይት እንደሚያደርጉና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር እንዲገባ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩም ገልፀዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የአስፓልት መንገድ ስራው በፍጥነት ከከተሞች እንዲጀመር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ከንቲባዎችና አስተዳዳሪዎች ጥሪ አቅርበዋል።
የጎሬ-ማሻ-ቴፒ አስፓልት መንገድ ስራ ፕሮጀክት አመራሮችና ባለሙያዎች በበኩላቸው ከተሞች አካባቢ ንብረት የማስነሳትና ከይገባኛል ነፃ የማድረግ ስራ በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት መዋቅሮች ተሠርቶ ከተጠናቀቀ በፍጥነት ማሽነሪዎችን በማስገባት የአስፓልት ግንባታ ስራውን ለመጀመር ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
