





በምዕራብ ኦሞ ዞን የዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በጋችት ወረዳ ቤሩ ቀበሌ የክልል እና የዞን የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ዞናዊ ማስጀመሪያ በዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
የተፋሰስ ልማት ሥራው “የአፈር ጥበቃ ስራችን ለብልፅግናችን” በሚል መሪ ሃሳብ በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች ላይ እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።
የክልል እና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ የወረዳ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የተፋሰስ ስራዎችን አስጀምረዋል።
የክልሉ የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ አለሙ ከስኩ እንደተናገሩት የአፈር እና ዉሃ እንዲሁም ደን ጥበቃ ላይ ሁሉም አርሶ አደሮች የበኩላቸውን ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ፓርቲው በባለፉት ወቅት በአፈር እና ዉሃ ጥበቃ እና በአረንጓዴ አሻራ በርካታ ሥራዎች ሰርቷል ነው ያሉት።
የክልሉ የግብርና ምክትል ሃላፊ አቶ ታመነ በቀለ በበኩላቸው እንደተናገሩት የምርት እና ምርታማነት ለመጨመር እና የተጎዱ መሬቶች ለመታደግ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተናግሯል።
የዞኑ የግብርና አካባቢ ጥበቃ መምሪያ ሃላፊ አቶ መልኬ ኬላኬ እንደተናገሩት፤ ዛሬ በተጀመረውና ለአንድ ወር በሚዘልቀው የተፋሰስ ልማት ሥራ ከ54 ሺህ 500ሄክታር በላይ የተራቆቱ አካባቢዎች የአፈርና የውሃ ጥበቃ ይከናወናል ብልዋል።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው የመሬት መራቆትን የሚቀንስና በጎርፍ የሚወሰድን አፈር የሚታደግ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአንድ ወር በሚቆየው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ላይ ከ150 ሺህ የሚሆኑ የዞኑ ነዋሪዎች በባለቤትነት እንደሚሳተፉ ተናግሯል።
በዞኑ ካሉት ቀበሌዎች 99 ቀበሌዎች በዛሬው የተቀናጀ የተፋሰስ ሥራ መጀመራቸውን አቶ መልኬ አስገንዝበዋል።
የጋችት ወረዳ ዋና አቶ ስንታየሁ ጋማሪ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የአካባቢውን ስነምህዳር ከመለወጥ በተጨማሪ ለምርታማነት እና ለኑሮ ምቹ አካባቢ መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት በቀበሌዎች ደረጃ የተጎዱ መሬቶች ትኩረት በማድረግና ከዚህ በፊት የተሰሩ የተፋሰስ ቦታዎች እንደገና የማደስ ስራዎች በስፋት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
እነዚህን የተገኙ ውጤቶች በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ወጣቶች ሴቶች እና የተለያዩ የህብረተሰቡ ክፍል በነቂስ ወጥቶ በልማቱ ላይ መሳተፍ ጀምሯል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
