የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ሠራተኞች ደንብ እና የገቢዎች ቢሮ የተርን ኦቨር ታክስና የቴምበር ቀረጥ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደረገ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ሠራተኞች ደንብ እና የገቢዎች ቢሮ የተርን ኦቨር ታክስና የቴምበር ቀረጥ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከክልሉ ምክር ቤት ባለድርሻ አካላት ጋር የግብዓት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረክ በታርጫ ከተማ ተደርጓል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ሰራተኞች ደንብና የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የተርን ኦቨር ታክስና የቴምበር ቀረጥ ረቂቅ አዋጅ ሰነድ ለባለድርሻ አካላት ቀርበው ማሻሻያ በሚያስፈልግበት ጉዳዮች ላይ ሀሳቢና አስተያየት ተነስተው የጋራ ውይይት ተደርጎበታል።

የገቢዎች ቢሮ የተርን ኦቨር ታክስና የቴምበር ቀረጥ ረቂቅ አዋጅ የክልሉ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን፣በምርትና መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ለማሻሻል፣በንግድ ግንኘነት ውስጥ ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ፣ተጨማሪ የእሴት ታክስ ያልተመዘገባቸው ሰዎች ግዴታቸውን እንዲወጡ፣የታክስ ስርዓት ሽፋን የተሟላ ለማድረግና በክልሉ የተዋሀደ የታክስ ስርዓት እንዲኖር በማስፈለጉ በፌዴራል አሁን ስራ ላይ ያለው የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ ጋር የተጣጣመ እና ከክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚሄድ አዋጅ በማስፈለጉ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ በወቅቱ እንዳሉት፤ በተቋማት የሚዘጋጁ ደንብና አዋጆች አስፈላጊነታቸው ታምኖበት በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገምግሞና ተተችቶ በክልሉ ምክር ቤት ጸድቀው ሥራ ላይ እንዲውሉ ይደረጋል ብለዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ሰራተኞች ደንብ እንደሀገር እየተደረገ ያለው የፍትህ ተቋማት ግንባታ የረፎርም ሥራዎች አካል እንደሆነም ያነሱት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕረዚዳንት አቶ ቆጭቶ ገ/ማሪያም ይህም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጠው የፍርድ ቤቶች ዳኝነት ነፃነት አንዱ መገለጫ እንደሆነም አስረድተዋል።

የክልሉን ገቢ የማመንጨት አቅም ታሳቢ ያደረገና በገቢ አሰባሰብ ወቅት የሚፈጠሩ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን በመፍታት የገቢ አቅም በማሳደግ የህዝቦች የልማት ጥያቄዎችን ለማሟላት የረቂቅ አዋጁ ጠቀሜታ የጎላ በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት የተሰበሰቡ ገንቢ ግብዓቶች የሪቂቅ አዋጁ አካል እንዲሆኑ ይሰራል ያሉት የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ ናቸው።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የክልሉን ወጪ በራስ አቅም ለመሸፈን ደንቢና አዋጆችን አውጥቶ የተለያዩ የገቢ መሰብሰቢያ ኮሪደር አማራጮችን በመጠቀም የክልሉን የገቢ አቅም ለማሳደግ እያደረገ ያለው ጠንካራ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የገለጹት የክልሉ ምክር ቤት በጀት፣ፋይናንስና ኦዲት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ የኋላሸት በላይነህ ተናግረዋል።

ከባለድርሻ አካላት ግብዓት የተሰበሰበው የገቢዎች ቢሮ ተርን ኦቨር ታክስና ቴምበር ቀረጥ ረቂቅ አዋጅ እና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ሠራተኞች ደንብና በክልሉ ምክር ቤት በ6ኛው ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የሚጸድቁ መሆናቸውም ተመላክቷል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *