በኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ የዳበረ የፖለቲካ ባህልና ሰፊ ምህዳር ተፈጥሯል – የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ

Spread the love

በኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ የዳበረ የፖለቲካ ባህልና ሰፊ ምህዳር ለመፍጠር የተደረገው ጥረት አበረታች መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ገለጹ።

በ2010 ዓ.ም የተመሰረተው የጋራ ምክር ቤቱ ፓርቲዎች በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በፖለቲካና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ ኢዜአ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለን አነጋግሯል።

በማብራሪያቸው ለውጡን ተከትሎ የዳበረ የፖለቲካ ባህልና ሰፊ ምህዳር ለመፍጠር የተደረገው ጥረት አበረታች መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ በሀሳብ የበላይነት የማመን ባህል እንዲጎለብት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል።

መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት የሚያስችሉ የፖሊሲና የህግ ማሻሻያዎችን ማድረጉ ለመጣው ውጤት ጉልህ ድርሻ እንዳለውም አስረድተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

በመሆኑም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተለይም በፖለቲካው መስክ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተሳትፎ መነቃቃት እንዲኖር አድርጓል ነው ያሉት።

የጋራ ምክር ቤቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሰባሰቡና እንዲመካከሩ መድረኮችን በመፍጠር በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እያደረገ ይገኛልም ብለዋል።

የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም በመንግስት ስልጣን ኃላፊነት ተሰጥቷቸው መስራታቸው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዲስ ባህል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር በማድረግ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረትም ፓርቲዎች ጉልህ ተሳትፎ እያደረጉ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 63 ሀገራዊና ክልላዊ ፓርቲዎችን ያቀፈ መሆኑ ይታወቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *