ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የታዳሽ ኃይል አከፋፋይ በመሆን ቀጣናውን አስተሳስራለች – አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር)

Spread the love

በተባበሩት ዐረብ ኢምሬት አቡዳቢ ከጥር 03 እስከ ጥር 04 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ “Powering Humanity: Renewable Energy for Shared Prosperity” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ በሚገኘው 16ኛው የዓለም አቀፉ የታዳሽ ኃይል ኤጀንሲ (IRENA) ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በቋሚ መልዕክተኛዋ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ተወክላ በመሳተፍ ላይ ትገኛለች።

አምባሳደር ጀማል በጉባኤው ባቀረቡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ መግለጫ፥ ሀገሪቱ የምትጠቀመው ኃይል ከ98 በመቶ በላይ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች የተገኘ መሆኑን፣ ሀገራችን ታዳሽ ኃይል ማመንጨት ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪካ የንጹህ ኃይል አከፋፋይ በመሆን ቀጣናውን ማስተሳሰሯን እንዲሁም በነዳጅ የሚሰሩ ተሽካርካሪዎች እንዳይገቡ በማገድ ከዓለም የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗን አንስተዋል።

ይህም የኢኮኖሚ ዕድገቷን ከካርቦን ልቀት ነፃ በሆነ መንገድ ለማረጋገጥ ያስቀመጠችውን ግብ ስኬታማነት የሚያሳይና ለሌሎች አዳጊ ሀገራትም እንደ ሞዴል የሚወሰድ ተሞክሮ መሆኑን አብራርተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ድምጽ ሆና እንደምትቀጥል አጽንኦት የሰጡት አምባሳደር ጀማል፥ እ.አ.አ በ2027 በአዲስ አበባ የሚካሄደው 32ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ሀገሪቱ በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ያላትን ግንባር ቀደም ሚና ከማጠናከር በዘለለ ለአዳጊ ሀገራት ፍትሐዊ የኃይል ሽግግር እንዲረጋገጥ እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድጋፎች እንዲሳለጡ ትልቅ ዕድል መሆኑንም አስምረውበታል።

አምባሳደር ጀማል ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት እና ኩባንያዎች ኃላፊዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።

ውይይቶቹ የኢትዮጵያን የታዳሽ ኃይል መሠረተ ልማት የማስፋፊያ ግንባታዎችን እንዲሁም ለኮፕ32 ጉባኤ ስኬት ድጋፍ ማሰባሰብ ላይ ያተኮሩ እንደነበሩ ኤምባሲው ለኢቢሲ የላከው መረጃ ያመለክታል።

ዓለም አቀፉ የታዳሽ ኃይል ኤጀንሲ (IRENA) እ.አ.አ. ጃንዋሪ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በጀርመን ቦን ከተማ ታዳሽ ኃይል ላይ ትኩረቱን በማድረግ ለሀገራት የቴክኒክ ዕውቀትና የፖሊሲ ምክር የሚሰጥ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ተቋም በመሆን የተመሰረተ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የማቋቋሚያ ስምምነቱን በመፈረም መሥራች አባል መሆኗ ይታወቃል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *