የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ይበልጥ በሚያጎላ መልኩ ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል- ብሔራዊ የዝግጅት ኮሚቴ

Spread the love

38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ይበልጥ በሚያጎላ መልኩ ለማስተናገድ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።

ጉባኤውን በስኬት ለማከናወን 35 ተቋማትን ይዞ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ የቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቂያ በተመለከተ በጋራ ማብራሪያ ሰጥቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና የኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንዳሉት፣ ለ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 46ኛው የስራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ በቂ ዝግጅት ተደርጎበታል።

የዘንድሮው የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ይበልጥ በሚያጎላ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶ ዝግጅት የተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ማረጋገጥ የሚችሉ ከ40 በላይ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን ማስተናገዷን ተናግረዋል።

ለ38ኛው የህብረቱ ጉባኤም ኢትዮጵያ እንደ አባልና አስተናጋጅ ሀገር ዝግጅቱ ግልጽ አካሄድ እንዲኖረው ማኑዋል ማዘጋጀቷንን ነው ያብራሩት።

የመረጃ ክፍተት እንዳይፈጠር በእንግሊዘኛ፣ በአረብኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋ የሰለጠኑ በጎ ፈቃደኛ ካዴቶችን በማሰልጠን ስምሪት እንዲወስዱ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

ለሆቴል፣ ለትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች ተገቢውን ግንዛቤ መፈጠሩንም ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ፌደራል እና የአዲስአበባ ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃ የእንግዶችን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውንም ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ፣ የውሀ፣ የቴሌኮምና መሰል አገልግሎቶችን በቅልጥፍና መስጠት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ በልዩ ሳሎን እና በመደበኛው ተርሚናል በቂ የሰው ሃይል የተመደበ ሲሆን በዚህም እንግዶች ቀልጣፋ የኢሚግሬሽንና የጉምሩክ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኙ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በኩል ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።

የቻርተር አውሮፕላን ይዘው ለሚመጡ እንግዶች የመደበኛውን በረራ በማያስተጓጉል መልኩ በቂ የአውሮፕላኖች ማቆያ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *