በህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ላይ የህግ በላይነት ለማረጋገጥ ይሰራል፦ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት “ህገወጥ ንግድና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመከላከል በጋራ እንተጋለን!” በሚል መሪ ቃል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቦንጋ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በዉይይት መድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ መበራከት በክልሉ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና የፖለቲካ ያለመረጋጋት እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በህገወጥነት የተሳተፉትን ተጠያቂ ማድረግ እና የህግ በላይነት ማስከበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የባለድርሻ አካላት ውይይትና ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ የመረጃ ስርዓት ማጠናከርና የጥቆማ ስርዓት መዘርጋት የህግ በላይነትን ለማስከበር ጉልህ ሚና እንዳለው ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል ።

ህገወጥ ማደያዎችና ነጋዴዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ፣ ማደያዎች ባሉበት አካባቢ የነዳጅ ችርቻሮ ማስቆም፣ ተገቢ የሆነ የቁጥጥር ስርዓቱን በመዘርጋት በአግባቡ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል ።

በክልሉ ውስጥ ያሉ ኬላዎች ከተቋቋሙበት ዓላማ ዉጭ ገቢ በመሰብሰብ በሸማቹ ማህበረሰብ ላይ ዋጋውን በመጨመር የኑሮ ውድነት እንዲባባስ አስተዋጽኦ እያበረከቱ በመሆኑ ይህ መታረም እንዳለበት አቅጣጫ ርዕሰ መስተዳድሩ አስቀምጠዋል ።

በንግዱ ስርዓት የሚከሰተው የኮንትሮባንድ ይዘት ተለዋዋጭና ውስብስብ በመሆኑ በተቀመጠው የህግ ማዕቀፍ ለመምራት የባለድርሻ አካላት ምክክር፣ ቅንጅትና ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል ።

የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቆጭቶ ገ/ማሪያም ኮንትሮባንድና የሸማቾች ጥበቃ ህግ ፍ/ቤቱ በትኩረት ከሚሰራባቸው ጉዳዮች አንዱ በመሆኑ የህብረተሰብ ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር ህግን ለማስከበር በቅንጅትና በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አንስተዋል ።

የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ የኮንትሮባንድ መስፋፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ አካሄዱን እየቀየረ ስለመጣ የግብረ ኃይሉ ተቀናጅቶ ህግን ማስከበር እንዳለበት ተናግረዋል።

የነዳጅ አቅርቦትና ግብይት ስርዓት ላይ የሚከሰተው ህገወጥነትና ኮንትሮባንድ አጠቃላይ የንግድ ስርዓቱንና ማክሮ ኢኮኖሚውን ስለሚያዛባ ግብረሃይሉ በጥብቅ መከታተል፣ መቆጣጠርና እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ አቶ ተመስገን ከበደ ገልጸዋል ።

በመድረኩ ላይ በክልሉ ህገወጥ የንግድና ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር እየተሰራ ቢሆንም ህገወጥነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን በማስታወስ ለመግታት የተቀናጀና ወጥነት ያለው እርምጃ መውሰድና ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚገባ ተነስቷል ።

በመድረኩ ላይ ከክልል እስከ ዞን ባለዉ የሚመለከታቸዉ የግብረ ኃይሉ አባላት ተሳትፈዋል።

በጌታሁን ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *