የክልሉ መንግሥት የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ከመገምገም ባሻገር ቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ በመወያየት አቅጣጫ አስቀምጧል።የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳች ቢሮ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የክልሉ መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት 1ኛው ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ አድርጎ ያስቀመጣቸው ጉዳዮችን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

የክልሉ መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት 1ኛው ግማሽ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማንን ጨምሮ የክልልና የዞን አስተባባሪ አካላት፣የከተማ ከንቲባዎች እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ከጥር 27-29/2017 መገምገሙን አስታዉሰዋል።

ግምገማውን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ምክትል ቢሮ ኃላፊና የመረጃ ማዕከልና ዲጂታል ሚዲያ አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር መስፊን ወዳጆ፤በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት በ1ኛው ግማሽ ወራት በማህበራዊ ፤ኢኮኖሚ፣በመሠረተ-ልማትና በአስተዳደር ዘርፎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

አመራሩ በተሰማራበት የአመራርነት መስክ ውጤታማ አፈጻጸም በማስመዝገብ የብልጽግና ጉዞ እንዲያስቀጥልና ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን መፍታት የሚችሉ አመራሮችን ለማፍራት የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎች መሰራቱን ዶ/ር መስፍን ወዳጆ ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ ከክልል ማዕከል ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን የመገምገምና የማጥራት ሥራ መከናወኑንም ኃላፊው አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ በግማሽ ወራት ሰላምና ጸጥታ የማስፈን፣የጸረ ሙስና ትግልና በፐቭሊክ ሰርቪስ ሪፎርም ስራዎች መጀመራቸዉን ኃላፊዉ አመልክተዋል።

በኢኮኖሚ ዘርፍ የግብርና ኢኮኖሚ አቅሞችን በመለየት ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር እና በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው እንቅስቃሴ በተለይም በሌማት ትሩፋት እንሼቲቭ በዶሮ እርባታ፣በከብት፣ዓሳ ልማትና በሌሎች የተጀመሩ ተግባራት ጥሩ ቢሆንም ክልሉ ካለው አቅም አንጻር አሁንም ትኩረት እንዲሰጥ መገምገሙን ገልጸዋል።

ሌላው በመኸር እና በጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣በከተማ ግብርና፣በአረንጓዴ አሻራ ኢንሼቲቭ የተመዘገቡ ውጤቶች ሊጠናከር የሚገባው ሲሆን አሁንም ከአፈር ማዳበሪያ አስተዳደርና ዕዳ አመላለስ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተት እንዲሻሻል ተጠይቋል።

የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት ሥራዎች በግማሽ ዓመቱ የታጠና ያልታጠበ ቡና አጠቃላይ 25ሺህ 247 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረብ መቻሉንም በመግለጫቸው አመላክቷል።

በቅመማ ቅመም ኮሪሪማ፣እርድ፣ዝንጅብል፣በርበሬና ቁንዶ በርበሬ፣ጥምዝ ምርት ክልሉ ትልቁን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን በበጀት ዓመቱ 21 ሺህ 877 ቶን የተለያየ ዓይነት ያላቸው የቅመማ ቅመም እና የሻይ ምርት ለውጭ እና ለሀገር ውስጥ ገበያ 2813 ቶን ማቅረብ እንደተቻለም አብራርተዋል።

በማዕድን ሀብት ልማት የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች ያሉ ሲሆን ቀጣይ የተቀናጀ ግብረሃይል በማቋቋም የሚስተዋሉ ህገወጥ ንግድና ግብይት እንዲሁም ዝውውር ማስቆም በትኩረት መሰራት የሚገባዉ መሆኑንም አንስተዋል።

የክልሉን ህዝብ የመልማት ፍላጎት ለመሙላት የተለያዩ ገቢ አማራጮችን አሟጦ በመጠቀም ቀጥተኛ ባልሆኑ ታክሶች እና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል።

የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት በማሻሻል የክልሉን ገቢ ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራት አበረታች ቢሆንም በከተሞች የገቢ መሠረት በማስፋት ገቢን አሟጦ መሰብሰብ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ በየደረጃው ያለው አመራር ቅንጅት መጠናከር እንዳለበትም አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ በክልሉ ያለውን ሰፊ የመሠረተ ልማት ክፍተቶችን ለማሟላት በክልሉ መንግስትና በህብረተሰብ ተሳትፎ የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራዎች እንደተሰሩም በመግለፅ አሁንም የመንገድ ከፈታና ጥገና፣የቦይና ዲች እንዲሁም በትራንስፖርት አገልግሎት ትርፍ መጫን፣ክፊያ፣የትራፊክ አደጋ መከላከልና የመናኸሪያ ፕሮጀክት አፈጻጸሞች ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጉ ጉዳዮች ናቸው።

በክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ለማሳደግ ተጀምረው የተቋረጡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ በተሰራው ሥራ የክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን 43.73% ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

በከተማ ልማት በክልሉ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራዎች ተስፋ ሰጪ እንደሆነ መገምገሙን ጠቅሰው በቀጣይም ለስራው አስፈላጊ የበጀት ምንጭ መለየት፣የህብረተሰብ ተሳትፎ ማሳደግ፣የሚገነቡ ቤቶች ፕላን እና የጥራት ደረጃ ማስጠበቅ እንደሚገባና ሳይፈቀዱ የተያዙ የከተማ መሬቶችን ህጋዊ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች እንዲጠናከርም ተጠይቋል።

በማህበራዊ ዘርፍ የትምህርት ልማት ሥራዎችን ተደራሽ በማድረግ የትምህርት ስብራት ለመጠገን ”ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ” በህብረተሰብ ተሳትፎ እና በመንግስት ትኩረት የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻል፣የውስጥ ቁሳቁስ ማሟላት እና በትምህርት ቤቶች የምገባ አገልግሎት ማስጀመር ተችሏል።

የተጀመረው የምገባ አገልግሎት ማስፋት፣አዳሪ ትምህርት ቤት፣ሞዴል ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤት ግንባታ እና ከመምህራን ደመወዝ መዘገየትና ለሌሎች ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጥ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።

በጤናው ዘርፍ የወባ ወረርሽን መከላከልና መቆጣጠር ፣የጤና ተቋማት ግንባታ፣የቲቪ እና የኤች አይቭ ኤድስ በሽታ እንዲሁም የእናቶችና የህጻናት ጤና አገልግሎት የተጀመሩ ሥራዎች የሚበረታታ መሆኑና ቀጣይ ህገወጥ መድኃኒት ቁጥጥርና ግብይት መከላከል ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ተብለዋል።

ዘላቂ ክህሎት መሪ የስራ ዕድል በመፍጠር የዜጎች ተጠቃሚነት የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ በገንዘብና

መሬት አቅርቦት የተጀመሩ ሥራዎች በልዩ ትኩረት እንዲመሩ አጽንኦት መሰጠቱን አንስተዋል።

የክልሉ የቱሪዝም አለኝታዎችን በመለየትና በመጠበቅ መዳረሻዎችን የመልማትና ለማስፋት የተጀመሩ ሥራዎች እንዲጠናከርም ተመላክቷል።

የክልሉ መንግስት የበጀት ዓመቱ 1ኛው ግማሽ ዓመት የተቋማት የተግባር አፈጻጸም በጥልቀት በመገምገም ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ያስቀመጠ ሲሆን ተቋማትም ጠንካራ ጎኖችን በማጠናከር ክፍተቶችን በመለየት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የክልሉ መንግሥት ከአፈጻጸም ግምገማ ባሻገር ከእምቅ አቅም ወደ ሚጨበጥ ሃብት በሚል መሪ የቀጣይ ሶስት ዓመት ክልላዊ የፖለቲካና የልማት አቅጣጫዎች ላይ ተወያይተዋል ብለዋል።

በመንግሥት ተቋማት በመደበኛነት ከሚከናወኑ ተግባራት ባሻገር ብዛትን ጥራትን ፈጠራንና ፍጥነትን መነሻ ያደረ የሰላም፣ልማትና የመልካም አስተዳደር አንኳር ጉዳዮች በትኩረት እንዲሰሩ ተወያይተው አስቀምጧል።

እነዚህም የፖለቲካ እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች፣የአገልግሎት አሰጣጥ መፍታት፣የግብርና እና የገጠር ልማት ተግባራት፣የአረንጓዴ አሻራ፣የአርሶ አደር ቁጠባና ብድር ሥርዓት፣ ሰላምና ፀጥታ፣የስራ ዕድል ፈጠራ፣የኑሮ ውድነት ቅነሳ፣የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማትና የክረምና የበጋ በጎ አገልግሎት ሥራዎች ናቸው።

የክልሉ መንግስት ሀገራዊ ኢንሼቲቭ ባሻገር በክልላዊ ኢንሼቲቭ በንቅናቄ መመራት የሚገቡ በተለይም የቡና፣ሻይና ቅመማቅመም ልማት፣የአትክልትና ፍራፍሬ፣እንሰት ተክል ማስፋት፣የወተትና የቅቤ መንደሮች፣አሲዳማ አፈር በኖራ ማከም ፣የግብዓት ዕዳ ማስመለስ፣ከተረጂነት መላቀቅ፣ማዕድን ልማት፣ ኢንቨስትመንት የማህበረሰብ ተሳትፎ ማሳደግና የቤተሰብ ዕቅድ ዝግጅትና ሌሎች የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ዶክተር መስፍን ወዳጆ ተናግረዋል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *