




በዳውሮ ዞን ማሪ ማንሳ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች፣ በተናጠል ከሚያካሂዱት እርሻ ወጥተው በኩታ ገጠም (ክላስተር) በመደራጀት የስንዴና ገብስ ምርታቸውን በእጅጉ ማሳደግ መቻላቸውን ተናገሩ። ይህ አዲስ የአሰራር ስርዓት፣ የባለሙያ ድጋፍን ከማቀለሉም በላይ እንደ አረም ያሉ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት በማስቻሉ “የልፋታችንን ዋጋ አግኝተንበታል” ሲሉ አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል ።
በወረዳው ዳካ የሊ ቀበሌ በሚገኘው “ቦካ ክላስተር” እንደተስተዋለው፣ ቀደም ሲል ተበታትኖ ይመረት የነበረው ማሳ አሁን በአንድ ላይ ተሰባስቦ በዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ሲለማ፣ የምርት መጠኑ ብቻ ሳይሆን ጥራቱም የላቀ ሆኗል።
የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ ከበደ እንደገለጹት፣ በወረዳው ከ6,700 ሄክታር በላይ መሬት በመኸር የለማ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ወደ 1,500 ሄክታር የሚጠጋው በክላስተር እና “በሙሉ ፓኬጅ” ቴክኖሎጂ የታገዘ ነው። ይህም ማለት አርሶ አደሮቹ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርት ስብሰባ ድረስ የምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያና የባለሙያ ድጋፍ በተቀናጀ መልኩ እንዲያገኙ ተደርጓል።
ኃላፊው አክለውም፣ “የምርት ብክነትን ለመቀነስ ከአካባቢው ትምህርት ቤቶችና ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ጋር በመተባበር ጊዜያዊ ማካማቻዎችን እያዘጋጀን ነው” በማለት ስኬቱ ዘላቂ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህ የልማት ሞዴል በቀጥታ ተሳታፊ የሆኑት አርሶ አደሮች፣ የኩታ ገጠም እርሻ ህይወታቸውን እንደለወጠው በደስታ ይናገራሉ።
“ከዚህ በፊት ብቻችንን ስንሰራ የባለሙያ ድጋፍ ማግኘትም ሆነ ግብዓት በጊዜው ማግኘት ፈታኝ ነበር” የሚሉት አርሶ አደሮቹ፣ “አሁን ግን በአንድ ላይ ስለሆንን ባለሙያዎች በቀላሉ ያገኙናል፤ የአረም ቁጥጥርና ሌሎች እንክብካቤዎችንም በጋራ እንሰራለን። በዚህም ከቤት ፍጆታ አልፈን ምርታችንን ለገበያ በማቅረብ ልጆቻችንን ለማስተማር በቅተናል” ሲሉ ገልጸዋል።
የግብርና ባለሙያው አቶ አፍራስ አልዳዳ በበኩላቸው፣ ባለፉት ዓመታት አሲዳማ አፈርን በኖራ የማከም ቴክኖሎጂ በመተግበሩ ምርታማነት መጨመሩን አስታውሰው፣ የቦካ ክላስተር ስኬት በሌሎችም አካባቢዎች ተሞክሮ እንደሚወሰድ አረጋግጠዋል።
አርሶ አደሮቹ ዘንድሮ ከዓምናው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ በታላቅ ተስፋ ገልጸው፣ የኩታ ገጠም እርሻ ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የማህበራዊ ትስስርንና የመረዳዳት ባህልን እንዳጠናከረላቸውም ተናግረዋል።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
