







በመርሀ ግብሩ ላይ የፓርቲያችን ምክትል ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የዋና ፅ/ቤቱ የዘርፍ ሀላፊዎች እንዲሁም የክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
በፕሮግራሙ ጅማሮ ላይ በቅርቡ በድንገተኛ ህልፈት ላጣናቸው ለፓርቲያችን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ ለነበሩት ለአቶ ተዘራ ወ/ማሪያም የህሊና ፀሎት ተደርጓል።
ለ3 ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚህ መርሀ ግብር ላይ ባለፉት 9 ወራት እንደ ፓርቲ በፖለቲካ፣በአደረጃጀት፣በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ፣በህዝብ እና አለም አቀፍ ግንኙነት፣በጥናትና ምርምር እንዲሁም በሀብት አስተዳደር ዘርፎች የተሰሩ ስራዎች ይገመገማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የፓርቲያችን ምክትል ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ አደም ፋራህ ቅቡልነት ያለው የሀገረ መንግስት ስርአት ለመገንባት እንዲሁም የሕዝቡን ተሳትፎ፣ ተጠቃሚነትና ብሎም እርካታን ለማረጋገጥ ባለፉት 9 ወራት በየደረጃው በሚገኙ የብልፅግና ፓርቲ መዋቅሮች በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል።
በተለይም የውስጠ ዴሞክራሲ ባህል ደረጃ፣የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት፣ባለፉት 6 የለውጥ አመታት የተገኙ የለውጥ እምርታዎች፣በምርጫ ማግስት ለህዝባችን ቃል የገባናቸው ጉዳዮች የተፈፃሚነታቸው ደረጃ በምን አይነት እርከን ላይ እንደሚገኝ፣በአምስቱ ሀገራዊ የልማት የትኩረት መስኮች የተገኙ ውጤቶች፣የብሔራዊነት ትርክትን እንደ ሀገር ለመገንባት የሄድንባቸው ርቀቶች እንዲሁም የ2ኛ መደበኛ ጉባኤ ዝግጅት በልዩ ትኩረት ምልከታ እንደሚደረግባቸው ገልፀዋል።
የፓርቲውን አፈፃፀም በጋራ መገምገም ያለንበትን ደረጃ ለመለየትና በቀጣይ የተግባራትን ስኬታማነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንዲሁም ዉጤታማ የክትትልና ድጋፍ ሥርአት ለመዘርጋት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር እንደሚያግዝም ጠቅሰዋል።
በዘርፎች የተከናወኑ የ9ወራት ሪፖርት፣የተጠናቀቁ የፓርቲ መመሪያዎች እንዲሁም የ2017 በጀት አመት ቅድመ ዝግጅት መነሻ አቅጣጫዎች በመርሀ ግብሩ ላይ እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።
