



በዳውሮ ዞን ቶጫ ወረዳ በኦክሊ-ዳልባ ቀበሌ በጥምር ግብርና አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የተሠማሩ አርሶ አደሮች መካከል ሞዴል አርሶአደር አቶ አለማየሁ ድልቦ እና ተይበላ ዶራሞ እንደተናገሩት፤
በበጋ መስኖ አትክልትና ፍራፍሬ ማልማት አይቻልም የሚለው አመለካከት ተቀይሮ በአንድ ማሳ ጥምዝ፣ ኮረሩማ፣ ድንች፣ ቲማቲም እና በቆሎ በማምረት ላይ መሰማራታቸውን አንስተዋል።
አርሶ አደሮቹ በሌላ በኩል አቦካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ ቡርቱካን፣ ሎሚ እና ሸንኮራ አገዳን በስፋት በማምረት ወደ ማዕከላዊ ገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
የአከባቢውን ምቹ ሁኔታን በመጠቀም ብዙ መስራት ስጠበቅ አለመስራቱ ቁጭት መፍጠራቸውን ገልፀው በበጋ መስኖ አትክልትና ፍራፍሬን በማልማት ኑሮኣቸውን በማሻሻል ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በስፋት ከዚህም በላይ በስፋት ለማምረት የባለሙያዎች ምክር፣ የውሃ ፓምፕ፣ አፈር መዳበሪያ፣ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ዝርያዎችን ፣ መስኖ አውታር እና ሌሎች ነገሮችን በማመቻቻት ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የኦክሊ-ዳልባ ቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ባቲሳ ባህሩ በበኩላቸው እንደተናገሩት ዝናብን ብቻ ጠብቀው በመዝራት ግብርናን ማዘመን እንደማይቻል በመግለፅ በየአከባቢያችን ያሉንን ፀጋዎች፣ ዕድሎች እና አቅሞች በመሰብሰብ በትጋት በመስራት ሁለንተናዊ ብልጽግናን መረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የቶጫ ወረዳ ግብርና አከባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ልማት ጽ/ቤት ም/ኃላፊ አቶ አንዷለም ኡሸቾ፤ ወረዳው በውሃ ሃብት የበለጸገ በመሆኑ ለዞኑም ጭምር ተስፋ ሰጪ በመሆኑ ከአትክልትና ፍራፍሬ በተጨማሪም የተለያዩ ጥራጥሬና እህልን በማልማት ውጤታማ መሆን ይቻላል ብለው ለዚህ ደግሞ ውሃው እንዳይባክን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።
አሁን በቅርቡ በቀጠናው በክልሉ ምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም/FSRP/ በጀት ድጋፍ በግንባታ ሂደት ላይ ያለው የጋሺ አነስተኛ መስኖ አውታር ሲጠናቀቅ ቀጠናውን ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አቶ አንዷለም አክለዋል።
በቀበሌው በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ-አደሮችን ለማበረታታት የባለሙያዎች ምክር፣ የግብአት አቅርቦትና መሣሪያ ድጋፍ ይደረጋልም መባሉን የቶጫ ወረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መረጃ ነው።
