


በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሚዛን አማን ከተማ በማህበረሰብ ተኮር ምክክር ዉጤታማነት ዙሪያ በሠላም ሚኒስቴር አማካይነት ለተከታታይ ሁለት ቀናት ሲሰጥ የቆየዉ የአሰልጣኞች ስልጠና ተጠናቋል።
በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከ6ቱም ዞኖች ለተወጣጡ የሠላምና ጸጥታ ተቋም ባለሙያዎችና የማህበረሰብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሙያተኞች የአመቻችነት ሥልጠና እንዲወስዱ የተደረገ ሲሆን በቀጣይ ተግባራት ውጤታማነት ዙሪያም አቅጣጫ ተቀምጧል።
የሥልጠናው ተሳትፊዎች በቆይታቸው በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ እና መስተካከል ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያም መክረዋል።
በዚህም የሠላም ጉዳይ ቅድሚያ ትኩረት ሊሠጠው የሚገባ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሥራው ውጤታማና ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ ከካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
አሁን ላይ ለሠላም እጦት ምክንያት ሆነው ጎልተው ከወጡ ጉዳዮች መካከል ሥራ አጥነት፣ የገበያ አለመረጋጋትና የእኔ ብቻ ይደመጥ የሚሉ ሐሳቦች በመኖራቸው ለነዚህ ጉዳዮች አስቀድሞ መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባ አንስተዋል።
ዉይይት ከተደረገባቸዉ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የማህበረሰብ ምክክር አመቻቾች ምን ዓይነት ክህሎት ሊኖራቸው እንደሚገባና ማህረሰብ ተኮር ምክክር በምን መንገድ ሲመራ ውጤታማ ይሆናል ፣እንዲሁም በለሎች ጉዳዮች ዙርያ ሰፋ ያለ ዉይይት ተደርጓል።
ምክክሩ ችግር ፈቺ ሆኖ በየአካባቢያችን ለሠላም እጦት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦች የሚነሱበት መግባባት ላይ ሊደረስ እንደሚገባ የገለጹት በሠላም ሚኒስቴር የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መብራቱ ካሳ አመቻቿች ለምክክሩ ውጤታማነት የገለልተኝነት ሚናቸውን እንዲወጡ እንዲሁም የተወያዮች ነጻነት እንዲጠበቅ አሳስበዋል።
በበጀት ዓመቱ 30 ሚሊየን ዜጎችን ተደራሽ ያደረገ የማህበረሰብ ምክክር እንደሚደረግ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል ሲል ማሻ ኤፍ ኤም ዘግቧል።
