




የኢትዮጰያን ፈጣን የአየር ትራንስፖርት እድገት እና እየሰፋ የመጣውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አለምአቀፍ ትስስር ዘላቂ ለማድረግ ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጉ መንገደኞችን በአመት የማስተናገድ አቅሙ ላይ ከደረሰው ከአዲስ አበባ ቦሌ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተጨማሪ አዲስ ሜጋ ጣቢያ እየለማ ይገኛል። ይኽ የተለያዩ አውሮፕላን ማረፊያዎችን የመገንባት ስትራቴጂ ኢትዮጵያን የወደፊቷ የአፍሪካ ግምባር ቀደም የአየር ትራንስፖርት በር የማድረግ አላማን ያነገበ ነው።
የቢሾፍቱ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ይሆናል። ይኽም ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ የኢንደስትሪ ማስፋፊያ አጀንዳ እና የረጅም ዘመን የአቪየሽን ስትራቴጂ ጋር የተናበበ ነው። ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድን አለምአቀፍ ተወዳዳሪነት ያጠናክራል። በAfCFTA ማህቀፍ የአፍሪካን የማገናኘት አቅም ይጨምራል። የንግድ እና ቱሪዝም ኮሪደሮችን ያሰፋል። ኢትዮጵያንም ቀዳሚ የበይነአኅጉር ማዕከል ያደርጋታል።
ከአዲስ አበባ ደቡብ ምስራቅ 40 ኪሎሜትር አካባቢ የምትገኘውና 1910 ሜትር ከፍታ ያላት ቢሾፍቱ ለአውሮፕላኖች ሥራ የተመቸ ከባቢ ያላት ሲሆን መዳረሻቸውን ኢትዮጵያ ላደረጉም ሆነ ለትራንዚት መንገደኞች ብቁ ሁኔታ ያላት ናት። ለመዲናችን ያላት ቅርበት ከነባሩ የአየር ትራንስፖርት ምኅዳር ጋር በቀላሉ የተዋሃደ አሠራር እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሥራ በአመት 60 ሚሊዮን ተጓዦችን የሚያስተናግድ ሲሆን ሲጠናቀቅም አፍሪካን ከአለም ቀዳሚ የአየር ትራንስፖርት መነኻሪያዎች አንዷ የሚያደርጋትን በአመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ላይ ይደርሳል።
