




በኮንታ ዞን ሀገራዊ ለውጥ እውን የሆነበት 8ኛ ዓመት የመጋቢት 24 የለውጥ ፍሬዎችን የሚደግፍ የድጋፍ ሰልፍ በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል።
በሰልፉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ረዳት የመንግስት ተጠሪና ፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነጋ አበራ በሀገሪቱ በሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎትና በነበሩ ውስጣዊና ውጫዊ ገፊ ምክንያት መጋቢት 24/2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ መምጣቱን ገልፀው በዚህም የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሪፎርሞች መደረጋቸውን አስረድተዋል።
የለውጡ መንግስት በርካታና ውስብስብ ፈተናዎችን እየተጋፈጠ አኩሪና እምርታዊ ድሎችን አስመዝግቧል ያሉት አቶ ነጋ ባለፉት ዓመታት ክልሉ ብሎም ዞኑ የለውጡ ፍሬ ሆነው ከተደራጁ ወዲህ የህዝብን የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል።
በተለይም የለውጡ መንግስት በኮንታ ዞኑ ያለውን እምቅ አቅም ወደ ልማት በመቀየር በዓለም ብራንድ እንዲትሆን አድርጓል ያሉት ረዳት የመንግስት ተጠሪው ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ከፊታችን የሚካሄደውን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም፣ በፍትሃዊነትና በዴሞክራሲያዊነት ለመፈፀም ለተጀመረው ስራ ህዝቡ የጎላ ሚናውን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ በበኩላቸው መጋቢት 24/2010 ዓ.ም የተበሰረው አዲስ የለውጥ ጉዞ ልዩ ልዩ ስብራቶችን በማከምና በመጠገን ባለፉት 8 ዓመታት በአፍሪካ ብሎም በዓለም የተመሰከሩ ተጨባጭ ውጤቶችን አስመዝግቧል ብለዋል።
ቀደም ሲል የነበረው ከፍተኛ የዕዳ ጫናና የተንኳሰሰ ዲፕሎማሲ ለመቀየር በፖለቲካው፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ ዘርፎች የተለያዩ ሪፎርሞችን በመተግበር ሰፊ ለውጦች መጥተዋል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በኮንታ ዞን ደረጃም በግብርናው፣ በቱሪዝሙ፣ በከተማ ማዘመን፣ በትምህርት፣ በጤና እና በተለያዩ መሠረተ ልማቶች አበረታች ውጤቶች መታየታቸውን አብራርተዋል።
የተመዘገቡ ድሎችን በማስቀጠልና ባልተፈቱ ጉዳዮች ላይ በማተኮር እየተተገበረ ያለውን የፍጥነትና ፈጠራ እሳቤ በማጠናከር የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ በጋራ እናፋጥናለን ያሉት አቶ ታከለ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ እንዲሆን መላው ህዝብ በጋራ መረባረብ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
በሰልፉ የክልል፣ የዞን፣ የከተማ አስተዳደርና የወረዳ አመራር አካላትን ጨምሮ የመንግስት ሰራተኞችና የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
