የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘዬ ማሻሻል ለመንግሥት ብቻ መተው የለበትም-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

Spread the love

የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘዬ ከነበረበት በማላቀቅ እንደሰለጠነው ዓለም ለማድረግ ከመንግሥት በተጨማሪ የግሉ ሴክተር እና ባለሀብቶች መተባበር እንደሚጠበቅባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በክረምት በጎፈቃድ መርሐ ግብር በሀላባ እና ከምባታ ዞኖች የተገነቡ ሞዴል የገጠር መንደሮችን አስረክበዋል።

በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ይህን የአኗኗር ዘዬ በኢትዮጵያ 50/60 በመቶ ብናደርሰው ከበለጸጉ ሀገራት አኗኗር ዘዬ ጋር አስተካከልነው ማለት ነው ብለዋል።

እኛ የጀመርናቸውን ማሳዎች ለማበራከትም ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይሆን በከተማ ያሉ ሀብታሞች፣በውጭ ሀገር ያሉ ዳያስፖራዎች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ኩባንያዎች የሚያጸድቅ ሥራ መሥራት ከፈለጉ ለነፍሳቸው እርካታ መስጠት ከፈለጉ ይህን ጉዳይ ማገዝ አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ቤቶቹ በጣም ውድ እንዳልሆኑ እና አብዛኛው የግንባታ ግብዓት ከአካባቢው የሚገኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከነበረው የተሻሉ ስለሆኑ ቤተሰብ ለመጠየቅ የሚመጣ ደስ ብሎት ያርፍባቸዋል፤ሁሉም አርሶ አደሮችም ይህ የአኗኗር ዘዬ ይገባቸዋል፤ለዚህ ደግሞ ቤቶቹን ለማበራከት መተጋገዝ ይገባል ብለዋል።

ቀበሌው፣ወረዳው፣ ዞኑ፣ክልሉ ዋና ሥራው የዜጎችን ሕይወት ማሻሻል መሆኑን አስገንዝበው፤ ሻል ያለ ሀብት ያላቸው ሰዎች ደግሞ ይህንን መደገፍ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ተጋግዘን ዕጅ አጠር የሆኑ የእኛን ሰዎች በመደገፍ ኑሯቸውን እናሻሽል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ዐቅም ብቻ ሳይሆን ዐይናቸውን በመግለጥ ብር የሚገኝበትን እና የኑሮ ዘዬ የሚሻሻልበትን መንገድ ማሳየት ይጠበቃል ሲሉም አመላክተዋል።

ይህ ሲሆን የኢትዮጵያ ብልጽግና ወደምናስበው ደረጃ ይመጣል ነው ያሉት።

ይህን ብናሰፋ እንደ ሀገር የኩራት ምንጭ፤እንደ ሀገር ያለመሰደድ፣በሀገር የመሥራት፣በሀገር የመኩራት ልምምድን የሚያሳድግ ስለሆነ ተባብረን እንድናሰፋው አደራ እላለሁ ብለዋል።

እንሥራ፤እንበርታ፤ ካልሠራን የሚመጣ ለውጥ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ተግተን ሥንሠራ ለውጥ ማምጣት እንደምንችል ታይቷል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ከተባበርን፣ከተጋን፣ከሠራን ውጤት ስለሚመጣ በዚያው መንፈስ አበክረን ቀን ከሌሊት በመልፋት የሀገራችንን ብልጽግና እንድናፋጥን የጀመርነውን መልካም ጅማሮ ከፍጻሜ እንድናደርስ ድህነትን ታሪክ እንድናደርግ፣ችግርን ታሪክ እንድናደርግ፣በሽታን ታሪክ እንድናደርግ አደራ ማለት እፈልጋለሁ ብለዋል።

አሁን የሠራነው ትራኮማን፣ተላላፊ በሽታዎችን፣ ከከብት የሚተላለፍ በሽታን ጨምሮ በርካታ ችግሮችን የሚያስቀር ስለሆነ፤ የተጀመረውን ለማስፋፋት እየተረዳዳን እየተደጋገፍን በትብብር ልንጓዝ ይገባል ብለዋል በንግግራቸው ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *