




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና በወረቀትና በኦላይን መሰጠት ጀምራል፡፡
የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደገላ ኤርገኖ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በቦንጋ ዩኒቨርስቲ በመገኘት ፈተናውን በይፋ አስጀምረዋል።
በዛሬው ዕለት የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲዎች ፈተናቸውን እየወሰዱ እንደሚገኙ ተጠቅሷል።
በዚሁም ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ተማሪዎች ራሳቸውን በእውቀት አዳብረው ለነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለ አበርክተው ለማድረግ ፈተናውን በርትተው እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።
ፕሮፌሰሩ ለተፈተኞች መልካም ውጤትን በመመኘት ተማሪዎች ሙሉ ትኩረታቸውን በፈተናው ላይ በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በስ-ነልቦና ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ተማሪዎችን ለፈተናው በተዘጋጁት ልክ ተረጋግተው እንዲሰሩና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ በማሳሰብ ለተማሪዎች መልካም ውጤት ተመኝተዋል።
የዘንድሮው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ከሰኔ 23-ሀምሌ 03/2017 ዓ/ም እንደሚሰጥ የገለጹት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ፥ በክልሉ 19ሺህ 127 ተማሪዎች በፈተናው እንደሚቀመጡና ከነዚህም ውስጥ 9ሺህ 758 የማህበራዊ ሳይንስ እንዲሁም ቀሪዎቹ 9ሺህ 369 ተማሪዎች የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች መኾናቸውን ተናግረዋል።
ፈተናው በሰላማዊ ሁኔታ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እየተከናወነ ነዉ ያሉት የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደገላ ኤርገኖ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አስቀድሞ የቅድመ ዝግጅት ስራ በመስራቱን ጠቅሰው በኦንላይን ለሚፈተኑ ተማሪዎች በቂ የኮምፒዩተርና የመፈተኛ አዳራሽ መዘጋጀቱንም አመልክተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
