

በፓሪስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በቱሪዝም መስክ የተሰማሩ ባለሙያዎችን እና ተቋማትን ያሳተፈ የቱሪዝም ማስተዋወቅ ኩነት አካሂዷል።
በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ማህሌት ሃይሉ በመርኃ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የበርካታ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ መስህብ ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው ሃብቱን ለማልማት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ትንበያን ዋቢ በማድረግም ኢትዮጵያ ከዓለም ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻዎች አንዷ እንደምትሆን አመልክተዋል።
በመርሃግብሩ የተሳተፉ አካላት ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ እና የቱሪዝም ማስተዋወቅ ስራዎችን እንዲደግፉ አምባሳደሯ ጥሪ አቅርበዋል።
ለተጓዥ ጎብኚዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችን እንደሚያደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
