







በመንግስት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥን ሰው ተኮር የማድረግና መልካም አስተዳደርን የማረጋገጥ ጉዳይ የፓርቲው ዋና ተግባር ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ማሞ ተናገሩ ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የ2016 የተግባር አፈጻጸምና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጀሙ ከተማ እየመከረ ነው።
በፓርቲው የአፈጻጸም ግምገማ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ማሞ ከክልሉ ምስረታ ወዲህ በተከናወኑ የፖለቲካ ስራዎች በክልሉ ዉጤቶች መምጣታቸዉን ተናግረዋል ።
በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በተሰራው የፓርቲ ተልዕኮ የፓርቲውን ተልዕኮ የመፈጸምና ማስፈጸም የሚችሉ የአመራርና የአባላት አቅም እየጎለበተ መምጣቱንም ተናግረዋል ።
በዚህም በተከናወኑ ስራዎች በክልሉ 542 ሺህ የሚሆኑ አባላት መኖራቸውንም አቶ ጸጋዬ ማሞ በመድረኩ ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተከናወነው የልማት ስራዎች ስኬቶች የተመዘገቡበት እና ክልላዊ የሰላምና ጸጥታ ስራዎች አስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረሱንም ተናግረዋል ።
የአገልግሎት አሰጣጥን ሰው ተኮር የማድረግና መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ እንዲሁም የስራ ዕድል ፈጠራ፣የኑሮ ውድነትን መቀነስና ክልላዊ ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳይ የፓርቲው ዋና ተግባር ሆኖ የሚሰራ ይሆናልም ብለዋል አቶ ጸጋዬ ማሞ።
መድረኩ በዋናነት ክልላዊ የፖለቲካ ፣የመልካም አስተዳደርና የልማት ስራዎች አፈጻጸማቸውን ትኩረት ያደረገ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመት በእነዚህ ተግባራት ላይ አቅምን አሟጦ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን አመራሩ ትርጉም ባለው መንገድ ምላሽ ለመስጠት ከወትሮው በተለየ ዝግጁ ሊሆን እንደሚገባም አቶ ጸጋዬ ማሞ አሳስበዋል ።
የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ኬኒ ባስተላለፉት መልዕክት የብልጽግና ፓርቲ ቃልን በተግባር የመለወጥ መርህን ተከትሎ ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ እንደሚገኝም ተናግረዋል ።
ሕብረብሔራዊነት፣ወንድማማችነት እና እህትማማችነትን በማጠናከርም በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል ።
የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ የአፈጻጸም መድረክም በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች በመሬት መንሸራተት እና በናዳ ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የህሊና ጸሎት በማድረግ ተጀምሯል።
በመድረኩ አቶ ጸጋዬ ማሞን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣የዞን፣የወረዳና የከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ተገኝተዋል ።
በመድረኩ በክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የተከናወኑ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የኃላፊ ልዩ አማካሪ በሆኑት በአቶ ሰይድ ኢብራሂም በመቅረብ ላይ ሲሆን የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የዲሞክራሲ ባህል ዘርፍ ኃላፊ በሆኑት በአቶ ግርማ ባሻ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት እንደሚደረግ ከወጣው የድርጊት መርሃግብር ማወቅ ተችሏል።
በታጠቅ አበበ
