በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ 278 ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያሏቸው ችግኞች እንደሚተከሉ ተገለጸ

Spread the love

በክልሉ 56.7 ሚሊዮን ችግኞች የሚተከልበት የአረንጓዴ አሻራ የበልግ ተከላ በይፋ ተጀምሯል ።

የበልግ አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በጉራፈርዳ ወረዳ ሴጋ ቀበሌ ተገኝተው አስጀምረዋል ።

በዚሁ የማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ ባሰሙት ንግግር በ2016 ዓ.ም በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በ3 ምዕራፎች እንደሚተከል አስታውቀዋል ።

በክልሉ የሚተከለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያሏቸው ችግኞች በበልግ፣በአንድ ጀምበርና በክረምት ወቅት እንደሚተከሉም ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።

በበልግ የተከላ ወቅት 56.7 ሚሊዮን ፣በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ 18.9 ሚሊዮን ቀሪ 202 ሚሊዮን ችግኞች በክረምቱ ተከላ ይከናወናሉ ብለዋል አቶ ማስረሻ በላቸው።

ከችግኝ ተከላው ጋር በተገናኘም 72 ሚሊዮን የቡና ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውንም አቶ ማስረሻ ተናግረዋል ።

እስካሁን በክልሉ በተተከለ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ የክልሉን የደን ሽፋን ከነበረበት 41 ከመቶ ወደ 42.7 ከመቶ ማድረስ መቻሉንም ተናግረዋል ።

የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ደግፌ ኩደን በበኩላቸው በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያሏቸው ችግኞች ላይ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ባለፉት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ወቅት በተከናወኑ ስራዎች የተራቆቱ አካባቢዎች ማገገም መቻላቸውን ያብራሩት አቶ ደግፌ ዘንድሮ በሚተከሉ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ከመትከል ባለፈ የመንከባከብ ስራዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል ።

የጉራፈርዳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታጋይ ኤልያስ በወረዳው 2.8 ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን እና ለበልግ ተከላ 120 ሺህ ለደንና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች ተዘጋጅተው እየተተከሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል ።

በተከላው የተሳተፉ የአከባቢው ነዋሪዎች ለችግኝ ተከላው ከወትሮው በተለየ መንገድ መዘጋጀታቸውንና የተተከሉትንም መንከባከብ ለማንም የሚተው ተግባር አይደለም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *