



ምዕራብ ኦሞ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከሚገኙ ዞኖች አንዱ ሲሆን ብዙ ባህሎች፣ወጎች፣ተፈጥሮ ሀብቶችና ለቱሪዝም ምቹ የሆኑ ድንቅ ገጸ በረከቶች ያሉት አካባቢ ነዉ።
ዞኑ ከፊል አርሶአደርና አርብቶአደር ማህበረሰቦች የሚገኙበት መልከ ብዙ ዞን ነዉ።
በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የብሔረሰቦች ቱባ ባህሎች በራሳቸው የቱሪዝም መስህብ መሆን የሚችሉ በመሆናቸዉ የማልማት፣የማስተዋወቅና የመንከባከብ ስራ ይፈልጋል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በአዲስ መልክ መደራጀቱ ካስገኛቸው በርካታ ጥቅሞች ባሻገር የክልሉ የቱሪዝም ሀብቶች ጎልተው እንዲወጡ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል ይለናል፡፡
በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የብሔረሰቦች ቱባ ባህሎች በራሳቸው የቱሪዝም መስህብ መሆን የሚችሉ ናቸው
በየዞኖቹ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን፣ ታሪካዊ ቅርሶችን እንዲሁም የማይዳሰሱ ትውፊቶችን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ በመጥቀስ፡፡
በርካታ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች በአግባቡ በማልማት ከዘርፉ የሚፈለገውን ያህል የኢኮኖሚዊ ጥቅም ለማግኘት እንደዞን ከወትሮው በተለየ መንገድ እየሰራ መሆኑን መምሪያ አስታዉቋል።
በክልሉ በአርብቶ አደር አካባቢ ያለውን ቱባ በህልና ተፈጥሯዊ እና ታርካዊ የቱሪዝም መስህቦችን በአግባቡ መጠቀምና መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት የምዕራብ ኦሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ቦኒ ሀየች በአርብቶ አደር አካባቢ ያለውን ባህላዊ ዕሴቶችን እና የቱሪዝም መስህብ ቦታዎችን በማልማት የዞኑን ህዝብ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከኢኮኖሚ ፋይዳው አንፃር የቱሪዝም ዘርፍ ሚናው የጎላ በመሆኑ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የኦሞ ብሔራዊ ፓርክና ሌሎች የተፈጥሮ፤ ባህላዊና ታርካዊ ሀብቶችን በማልማት ጎልተው እንዲወጡ ለማድረግ ሰፊ እየተሰራ ነው ያሉት ኃላፊው በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የብሔረሰቦች ቱባ ባህሎች በራሳቸው የቱሪዝም ቀልብ መሳብ የሚችሉ ናቸው ብለዋል።
የሱሪ ብሔረሰብ ዶንጋ ጨዋታና የመኤኒት ብሔረሰብ ባህላዊ ጭፈራ ከዞኑ የቱሪዝም ፀጋዎች መከከል ተጠቃሾች መሆናቸውን ጠቅሰው የሱሪ ብሔረሰብ በዞኑ የሚገኝ አርብቶ አደር ማህበረሰብ ሲሆን ለየት ያለ የሰውነት ሥዕል በመሳልና በዱላ በመታገል የሚታወቅ መሆኑን ያስረዱት አቶ ቦኒ “ዶንጋ” የሱሪ ህዝብ ባህላዊ እምነቶችንና ሥርዓቶችን ይዞ የበለፀገ ባህላዊ ቅርስ መሆኑን አብራርተዋል።
በምዕራብ ኦሞ ዞን ከ26 በላይ የተለዩ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ፣ የኣኩ ፏፏቴ፣ የዳል ፏፏቴ፣ ንፋስ በር እና የሱሪ ብሔረሰብ የዶንጋ ጨዋታ በሀር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ጎብኝዎች እየተጎበኙ መሆናቸውን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ ልዩ ልዩ የዱር እንሰሳትና ዕፅዋት ይገኙበታል ያሉት አቶ ቦኒ 75 አጥቢ እንስሳትንና 325 የአዕዋፍ ዓይነቶችን እንደያዘ የሚነገረው ይህ ብሔራዊ ፓርክ፣ ውድንቢዎች፣ የመጋላ ቆርኪ መንጋ፣ ሳላዎች፣ የሜዳ ፍየሎች እና ሌሎም አጥቢዎች እንደሚገኙበትም ገልፀዉ ውድንቢ በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ብቻ የሚገኝ የዱር እንሰሳ መሆኑን አስረድተዋል።
በዞኑ በጎርጌሻ ወረዳ የሽዋ ጂባቡ ፊል ውሃ፤ በመኤኒት ጎልዲያ ወረዳ ያርጣ ቀበሌ ፊል ውሃና በመኤኒት ጎልዲያ የሚገኝ ልዩ ጨው በተፈጥሮአዊ የቱርስት መዳረሻነት እንዲለሙ የተለዩ ቦታዎች መሆኑናቸውን የጠቆሙት ኃላፊው የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ በአካባቢው የሚታዩ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት ከሚደረገው ርብርብ ጎን ለጎን መስዕቦችን የማስተዋወቅ ስራ እንደዞን በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ለትውልድ እንዲተላለፉ በተገቢው በመለየት ሰንዶ የማስቀመጥ ስራ እየሠራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ቦኒ ዞኑ በአብዛኛው የአርብቶ አደር አካባቢ በመሆኑ ባህላዊና የተፈጥሮ መስህቦች መገኛ ስፍራዎች በሰፊው የመሰረተ ልማት ችግር ያለባቸው በመሆኑ ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚመለከተው ሁሉ እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።
