




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ከJustice for all PF ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር “ሀገር በቀል እውቀት ለግጭት አፈታትና ዘላቂ ሠላም ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እንዳሻው የምክር ቤቱ ዋና ተልዕኮ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማፅናትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነታቸውን እውን ማድረግ ነው ብለዋል።
ምክር ቤቱ ላለፉት ዓመታት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማምጣት በርካታ ስራዎችን ሠርቷል ብለዋል አቶ ተስፋዬ ።
የJustice for all PF ፕሮጀክት አማካሪ አቶ ደረጀ ሽመልስ ደርጅቱ ሀገር በቀል ተቋም ሆነው ከተመሠረት ጊዜ አንስቶ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ በህግ የበላይነትና ባህላዊ ግጭት አፈታት ተግባራትን ከተጠሪ ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሀገር በቀል ዕውቀት ለኢትዮጵያ ወሳኝ መሆኑን ተናግረው እስካሁን በመጣንባቸው ሂደቶች አረጋግጠናል ያሉት አማካሪው ላለፉት 6 ወራት ብቻ ባህላዊ ዳኝነቱ የፍርድ ቤቶችን ጫና ምን ያህል እንዳቀለለው ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።
ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጋር ውጤታማ ተግባራት እንደሚንከውን የስራ ኃላፊዎች ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብለው በሀገራችን ላይ የተከሰቱ እርስ በርስ ግጭቶች የተፈቱበት ተሞክሮን አቀናጅተን በክልሉ ውስጥ የሚስተዋሉ አለመግባባቶች በዘላቂነት በሚፈቱበት መንገድ እንደሚሰሩ አክለው ገልፀዋል።
የምክክር መነሻ ሰነድ በብሔረሰቦች ትስስርና ግጭት አፈታት ኤክስፐርት አቶ አበበ ገብሬ እየቀረበ ሲሆን በመድረኩም የተለያዩ የክልል ስራ ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ የፌዴራል ተቋማት ባለድርሻዎች፣ የ3ቱ ዞኖች ተወካዮችና ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
