በሩብ ዓመቱ በሁሉም ዘርፎች ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ የተሻሉ አፈጻጸሞች ተከናውኗል ፦ ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የ2018 በጀት ዓመት የ1ኛዉ ሩብ የመንግስት እና ፓርቲ ተግባራት ዕቅድ አፈጻጸም በቦንጋ ከተማ እየተገመገመ ይገኛል።

ግምገማዉን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በ1ኛዉ ሩብ ዓመት በሁሉም ዘርፎች ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ የተሻለ አፈጻጸሞች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በሩብ ዓመቱ ከዕቅዱ አኳያ በማህበራዊ ዘርፎች በተለይም በትምህርት፣ ጤና እና በሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን ይህን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

በግብርናዉ ዘርፍ የግብርና ክፍሌ ኢኮኖሚ ማሳደግ የሚያስችሉ በመኸር እርሻ ልማት የማሳ ሽፋን ማሳደግ፣ በሌማት ትሩፋት ፣ የሻይ ልማት ሥራዎችን ለማስፋት ችግኝ ዝግጅትና ተከላዎች መከናወናቸውንም አስረድተዋል።

በየጊዜው ከህዝብ የሚነሱ የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄዎችን መመለስ እንዲቻል የተከናወኑ ጅምር ሥራዎች እንዳሉትም ርዕሰ መስተዳድሩ አንስተዋል።

የመንግስትና የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ማሳለጥ የሚያስችል የመሶብ አንድ አገልግሎት ወደ ሥራ ማስገባት እንዲቻል የህንጻ ግንባታ መገባደዱን ጠቅሰዉ ይህም በቅርቡ ተመርቀዉ ወደ ተግባር እንዲገባ ሰፊ እርብርብ እየተደረገ ስለመሆኑን አብራርተዋል።

ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የክልሉን ዘላቂ ሠላምና ጸጥታ ማረጋገጥ እንዲያስችል የውጭና ውስጥ ስጋት ያለባቸው አከባቢዎችን በመለየት በየደረጃው አስፈላጊ የፀጥታ ሥራዎች በሰፊዉ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

በአንደኛዉ ሩብ ዓመት በጥንካሬ የታዩ አፈጻጸሞችን በማጎልበት፣ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮችን በመለየት በቀሪ ወራቶች ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በበጀት ዓመቱ በሁሉም ዘርፍ የህዝብን ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት የታቀዱ ዕቅዶች በተጨባጭ እንዲፈጸሙ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ የአመራር ክትትልና ድጋፍ ሥራ የሚጠናከር ይሆናልም ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ፤ ልዩ አማካሪ በሆኑት በአቶ አለማየሁ አይበራ የ2018 በጀት ዓመት የአንደኛዉ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በዝርዝር እየቀረበ ይገኛል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *