#ሪፖርታዥ

Spread the love

የቦንጋ ከተማ የቆሻሻ አስተዳደርና አወጋገድ ስርዓት ጅምር ተሞክሮ

የአንድ ማህበረሰብ ኑሮ ዘይቤ የሚመዘነው በደረሰበት የአስተሳሰብና የስልጣኔ ደረጃ መሆኑ ይታወቃል። የአኗኗር ዘይቤው ደግሞ አዕምሯዊና አካላዊ ጤንነቱ ላይ አወንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድርበታል።

ይህ ጉዳይ በቀጥታ ከሚያተኩሩባቸው ነጥቦች አንዱ የአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ነው። ዓለም ዛሬ ላይ በአንድ ድምፅ ከሚነጋገርበት ስጋቶች አንዱ በአካባቢ ብክለት የሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ እና የሚያስከትለው የጤና ጉዳት መሆኑ ግልፅ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከቅርብ ጊዜ ወድህ በሀገር ደረጃ  የ“ፅዱ ኢትዮጵያ” ንቅናቄ የተለየ ትርጉም ተሰጥቶት እየተመራ መሆኑ አይዘነጋም። በዛሬው ዝግጅታችን ሰዎች በብዛት በሚሰፍሩባቸው ከተሞች ዙሪያ አካባቢያቸውን የሚያፀዱበት ስራዎች ላይ የባለድርሻ አካላትን ሀሳብና ተሞክሮዎችን እናስቃኛችኋለን።

የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በየጊዜ የከተሞች ቆሻሻ መመንጨት አቅም እያደገ መምጣቱን ዘርፉን እያስተባበሩ ያሉት ተቋማት እና ግብረሰናይ ድርጅቶች ይገልጻሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ NABU ኢትዮጵያ በቦንጋ ከተማ ባካሄደው ጥናት ከተማው በዓመት 200 ሺህ ቶን ቆሻሻ እንደሚያመነጭ ጠቁሟል።

እውቀት የታከለበት የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አስተዳደር ስርዓት ባህል እንዲሆን ከክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ፣  ከጤና ቢሮ እንድሁም ከፋይናንስ ቢሮ ጋር በመቀናጀት እየሰሩ መሆኑን የገለጹት የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኢንጂነር አስራት ገ/ማሪያም ከተማው የማንቀሳቀሻ መሠረተ ልማት ለማሟላት የቆሻሻ መጠኑን እና አይነቱን አወቆ ዝግጅት እንዲያደርግ አስችሏል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ለሰርኩላር ኢኮኖሚ እድገት ያግዛል የተባለውን ቆሻሻ መልሶ አገልግሎት ላይ ለማዋል NABU ኢትዮጵያ ከመንግስት ተቋማት ጋር በመተባበር በቦንጋ ከተማ ጊዜያዊ የቆሻሻ ማሸጋገሪያ ሼዶችን ገንብቶ በየፈርጁ እንዲያስተዳድሩ ከማደረግ ባለፈ በመልሶ አገልግሎት ዘርፍ ለወጣቶችና ሴቶች ማህበራት የስራ ዕድል መፍጠሩን ዶ/ር ኢንጂነር አስራት ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ጥበቃ ጉዳይ የዓለም ትኩረት ከመሆኑም በላይ በመንግስት ኢኒሼቲቮች ልዩ ድጋፍ መደረጉ ምቹ ዕድል ይፈጥራል ያሉት ዶ/ር ኢንጂነር አስራት በክልሉ ባሉት 3 ዞኖች ላይ መሠረት ያደረገው NABU ኢትዮጵያ የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባዮስፌር ሪዘርቭ ባለበት አካባቢ ያሉ ከተሞችን አየር ንብረት ሚዛን ለመጠበቅ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ላይ ሳይንሳዊ እርምጃዎችን ወስዶ እጅግ ውጤታማ የሆነ ስራ እየሠራ ነው ብለዋል።

የቦንጋ ከተማ መናሀሪያ አካባቢን ጨምሮ ቆሻሻ በብዛት የሚመነጭባቸውን 6 መንደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 3 ጊዜያዊ የቆሻሻ ማሸጋገሪያ ሼዶች በNABU ኢትዮጵያ ድጋፍ ተገንብተው በማዘጋጃ ቤቱ እየተመራ የሚገኝ ሲሆን ወደ እነዝህ ስፍራዎች የሚያደርሱ የወጣቶች ማህበራት እየተደራጀ መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል።

የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር የማታለም ቸኮል በበኩላቸው  በቦንጋ ከተማ የተጀመረው የቆሻሻ ማስወገጃ ተግባርን ቀምረን ሌሎች የክልሉ ዋና ዋና ከተሞች ባለድርሻዎችን አሳትፈው በሚመሩበት ሂደት ላይ እየሰራን ነው ብለዋል።

ውጤታማ እና ቀጣይነት ላለው ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት የአደረጃጀቶች ሚና ጉልህ ነው ያሉት ኢንጂነር የማታለም ይህንኑን ከህብረተሰቡና ማዘጋጃ ቤት ጋር  መክረን  ቅድሚያ የሚሰጠውን ቦታ በመለየት በቦንጋ ከተማ ላይ ውጤታማነቱን አረጋግጠናል ነው ያሉት።

ይህን ተግባር በስርዓት ለመምራት በቢሯችን ተዘጋጅቶ በክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት ፀድቀው ተግባራዊ የሆነው ደንብ ቁጥር 38/2017 ግለሰቦችና ድርጅቶች አካባቢያቸውን 20 በ50 ራዲየስ እንዲያጸዱ ከማድረጉም በላይ አሠራሩ ቀጣይና የተደራጀ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል።

ህብረተሰቡ ግንዛቤ ወስዶ በየቤቱ ቆሻሻን የሚበሰብስ፣ የማይበሰብስ እና አካባቢን የሚበክል በማለት በተለያዩ ከረጢት እንዲያጠራቅሙ ተደርጎ ውጤት ታይቷል ያሉት ኢንጂነር የማታለም የቦንጋ ከተማ ማዘጋጃ ቤትም በተገነቡት የቆሻሻ ማሸጋገሪያ ጣቢያዎች ላይ ሠራተኞችን ቀጥሮ ማህበረሰቡን እያላመደ ነው ብለዋል።

በቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ድክመት በሚመጣ የጤና ችግር ብዙ ሀብትና ህይወት ይወድማል ያሉት ኢንጂነር የማታለም የከተሞች አደረጃጀትና አጋር አካላት ከወዲሁ የቦንጋ ከተማን እንቅስቃሴ በመቀመርና መሠረተ ልማት በማሟላት አመለካከቱን ያዘመነ እና አካባቢውን የሚያጸዳ ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር እንዲንቀሳቀሱ አሳስበዋል።

ከተሞችን ከማጽዳት ባሻገር የሚበሰቡት ቆሻሻዎችን የገቢ ምንጭ ለማድረግ በማህበራት የተደራጁ ሴቶች ኮምፖስት ማዳበሪያ እንዲያዘጋጁ መደረጉን የገለጹት ኃላፊው በተለምዶ ሃይላንድ ፕላስቲክ የሚባሉትን ደግሞ ለመልሶ አገልግሎት የሚፈጩ ማሽኖች በNABU በኩል ድጋፍ ተደርገው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ላይ የሚታየውን ክፍተት ስላየን ፕሮጀክት ቀርፀን ፈንድ አፈላልገን በቦንጋ ከተማ የሙከራ ተግባራትን አከናውነናል ያሉት የNABU ኢትዮጵያ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አስተባባሪ አቶ አሳዬ አለማየሁ ደረቅ ቆሻሻ ስንል ምንድነው? ምን ያክል በየከተማ ይመነጫል? የሚሉ ሀሳቦችን በጥናት አስደግፈን በመለየት ከመነሻ ጀምሮ እየተለየና እየተመዘነ ወደ ጊዜያዊ ማሸጋገሪያ እንዲገባ እየተደረገ ነው ያሉት።

ይህንኑ ተግባር ለማሳለጥ በአማካሪዎች ባስጠናነው ጥናት መሠረት ቦንጋ ከተማ በዓመት 200 ሺህ ቶን ቆሻሻ እንደሚመነጭ የታወቀ ሲሆን ከመልሶ መጠቀም ባሻገር ከአንዳንድ ግል ህክምና ተቋማት የሚወጡ አደገኛ ቆሻሻዎች ወደ ወንዝና ከተማ ዳር ደኖች እንዳይገቡ የአስተዳደር ስርዓቱን ማዘመን አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗል ይላሉ አቶ አሳዬ አክለው።

ይህን ጥናት ውጤት ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ነዋሪዎች በተገኙበት በውይይት አዳብረነዋል ያሉት አቶ አሳዬ ለተጠሪ ተቋማት የጥናት ሪፖርቱን አሰራጭተን የዕቅዳቸው አካል አድርገው እንደሰሩ መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል።

የፕላስቲክ ከረጢቶችን መልሶ ለኢንዱስትሪ ግብዓት መጠቀም የሚያስችል ማሽን ገዝተን ለተደራጁ ወጣቶች አዘጋጀተናል ያሉት አስተባባሪው ህፃናት ለአካባቢያቸው ነቁ ሆነው እንዲያድጉ በከተማው 3 ትምርት ቤቶች ላይ የግንዛቤ ሞጁል ከማዘጋጀት እስከ ክበባትና ችግኝ ማዘጋጀት ስራ እየሰራን ነው ብለዋል።

ማህበረሰባችን በተለምዶ መንገድ ላይ ቆሻሻ ተጥለው ሲያይ ትዝ የሚለው ማዛጋጃ ቤቱ ነው ያሉን አቶ አሳዬ ማዘጋጃና ሌሎች ተጠሪ ተቋማት ከማስተባበር ውጭ ብቻቸውን ምንም ናቸውና ሁሉም ዜጋ በኃላፊነት ከማስተዳደር ጀምሮ ሌሎችንም ተጠያቂ እስከማድረግ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።

ይህ ተግባር የቆሻሻ ማስወገጃ ስርዓት ብቻ ሳይሆን ለወደፊት የከተሞቹ ቆሻሻ ማመንጨት አቅሙን በጥናታዊ መረጃ ለመለየት ያግዛል ያሉት ኃላፊዎች ተደራጅተው ፕላስቲክ ከረጥቶችን ለመልሶ አገልግሎት የሚያውሉ ማህበራት ለትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ሰፊ የግብዓት አቅም ይሆናሉ ብለዋል።
ከተሞችን ለእይታ እና ለኑሮ ጽዱ ማድረግ የሁሉም ህብረተሰብ ርብርብ የሚጠይቅ ነው ያሉት ኃላፊዎች በቦንጋ ከተማ ላይ የተጀመረውን ምርጥ ተሞክሮ በማስፋት የክልሉ ዋና ዋና ከተሞች ዙሪያ መሠረት ያደረጉ ግብረሰናይ ድርጅቶች፣ ኢንቨስተሮች፣ ባለሀብቶች እና ነዋሪዎች እንድሁም ዘርፉን የሚያስተባብሩ መዋቅሮች ተቀናጅተው በቀላል አቅም ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በመጨረሻም የከተማ ነዋሪዎች አስፈላጊ የማጓጓዣ መሠረተ ልማቶች እስክሟሉላቸው ድረስ ቆሻሻን በየዘርፉ ለይተው በማከማቸት ወደ ተዘጋጀላቸው ማሸጋገሪያ ጣቢያዎች በማድረስ ጤናቸውን እንዲጠብቁና የከባቢያቸውን እይታ ማራኪ እንዲያደርጉ ጥሪ ተደርገውላቸዋል።

በአሻግሬ ገ/ወልድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *