“ኪሎንጋ “(ተስካር) በሱሪ ብሔረሰብ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?

ባለፉት ተከታታይ ወራት ‘’የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?’’ በሚል አምድ አጠቃላይ የክልሉን ገጽታ የሚያሳዩ እና የስድስቱ ዞኖች የተለያዩ ባህላዊ ይዘቶችን የዳሰሱ ጽሁፎችን እንደየቅደምተከተላቸው ለውድ አንባቢያን አጋርተናል፡፡ ዛሬ ደግሞ በዚሁ አምድ ስር በምዕራብ ኦሞ ዞን የሚገኘውን የሱሪ ብሔረሰብ የሀዘን መግለጫ የሆነውን “ኪሎንጋ”(ተስካርን ) ሊናስቃኛችሁ እንወዳለን።
የምዕራብ ኦሞ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከሚገኙ 6 ዞኖች አንዱ ነው። ዞኑ አራት ነባር ብሔረሰቦች ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔራሰቦች ጋር በጋራ ተስማምተው፣ ተጋብተውና ተጋምደው የሚኖሩበት ዞን ነው፡፡ እነዚህ ነባር ብሔረሰቦች የእራሳቸው የሆነ ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋና ሌሎች ባህላዊ ወጎች እና እሴቶች ያሏቸው ሲሆን ከእነዚህ ነባር ብሔረሰቦች አንዱ የሱሪ ብሔረሰብ ነው።
የሱሪ ብሔረሰብ በምዕራብ ኦሞ ዞን ሱሪ ወረዳ ይገኛል። የሱሪ ማህበረሰብ እንደማንኛውም ማህበረሰብ የእራሱን ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክና ሌሎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ወጎች እና እሴቶች እንዲሁም የአመጋገብ ፤የአለባበስ ፤የጋብቻ ፤የደስታ ፤የሀዘን እና ሌሎች ባህላዊ ሥርዓቶች አላቸው ።
የሱሪ ብሔረሰብ በውስጡ (ትርማጋ ፤ቻይ እና ባሌ) ጎሣዎች አሉት። በማህበረሰቡ ዘንድ ከሚደረጉ ባህላዊ ክዋኔዎች መካከል አንዱ የሀዘን መግለጫ የሆነው ” ኪሎንጋ” ነው።
ኪሎንጋ (ተስካር) በሱሪ ማህበረሰብ ዘንድ በዋናነት ባላባቶች ፤ጎሳ መሪዎች ፣ ትላልቅ እና ታዋቂ ሰዎች ሲሞቱ ለማስታወስ የሚደረግ ባህላዊ ክዋኔ ነው።
ኪሎንጋ በሱሪ ብሔረሰብ ዘንድ ከጥንት ጊዜያት ጀምሮ ሲደረግ የቆየ ሲሆን ቤተዘመድ ተሰብስቦ አንድ ላይ በመሆን ትልቅ ክብር ያላቸው ሰዎች የሞት መታሰቢያ እንዲሆን እና ያላቸውን ሀብት ለማሳየት የሚደረግ ባህላዊ ድርጊት ነው።
ኪሎንጋን የሚያዘጋጀው ቤተዘመድ ሲሆን ለሟቹ ቅርብ የሆኑ ትላልቅ ሰዎች፣ ባላባቶች እና የአከባቢው ሽማግሌዎች ቀን በመያዝ ቀጥሮ የሚሰጥ ሲሆን ሁሉም ነገር በቤተሰብ ተዘጋጅቶ ስያልቅ በዕለቱ ሁሉም ሰው ካለበት ተሰብስበው በጋራ ያከብራሉ ።
ኪሎንጋን ለማክበር የሚመጡ ቤተዘመዶችም ሲመጡ የተመረጡ እና ለዕርድ የሚሆኑ በሬዎች እና ወይፈኖችን በመያዝ ባህላዊ የሀዘን መግለጫ ጭፈራ እያሳዩ ካሉበት ጉዞ ይጀምራሉ። በጣም ከሩቅ አካባቢ የሚኖሩ ከሆነም በዕለቱ ለመድረስ ቀን ከሌሊት በመጓዝ በዋዜማው በመድረስ አብሮ ያከብራሉ ።
በኪሎንጋ ላይ ቤተዘመድ የሆነ ሰው እንዲሁም ያልሆነ ሰውም አይቀርም፤ ያለውን ወይፈኖች እና በሬዎችን በመያዝ ወደ ተዘጋጀበት ቤት በመሄድ ከቤተዘመዶቹ ጋር ያከብራል።


ኪሎንጋ ለማካሄድ ከሚዘጋጁ ነገሮች መካከል ባህላዊ መጠጥ ቦርዶ(ጌሶ) እና ስጋ ሲሆን በኪሎንጋ ዋዜማ ሀዘናቸውን ለመግለፅ ቤተዘመድ ብቻ በተገኙበት ከተሰበሰቡ በሬዎች መካከል ዕርድ በማድረግ በጋራ ይመገባሉ፡፡
በዚሁ በኪሎንጋው ዋዜማ ምሽት የሚታረዱ በሬዎች ቀድሞ በዘመዶች ተወስኖ የሚታወቅ ሲሆን የሟቹ ቅርብ ዘመድ ማለትም የታላቅ ወንድም ወይም አጎት በሬ ተመርጦ የሚታረድ ይሆናል።
በኪሎንጋው ቀን ዕርድ የማይደረግ ሲሆን ቤተዘመድ የሆኑ እንዲሁም ያልሆኑ ሰዎች ስለራሳቸው ሀብት በዘፈን መልክ ያለው ሽለላ በማድረግ በሬዎችን በዕለቱ የተዘጋጀ በረት ውስጥ ካዞሩአቸው በኃላ ባህላዊ ክዋኔ በማድረግ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ።
ኪሎንጋ በማህበረሰቡ ዘንድ ሁለት ትርጉም ያለው ሲሆን አንደኛው ሟቹን ሰው ለማስታወስ ሁለተኛው ደግሞ ሰዎች ምን ያህል በሬዎች እንዳላቸው የሀብት መጠናቸውን ለማሳየት የሚዘጋጅ ሲሆን በሱሪ ማህበረሰብ በሬ ትልቅ ቦታ እንዳለውም አባቶች ይናገራሉ።
በዕለቱ ሁሉም ካለበት ይዞ የመጣውን በሬዎችን በማስቀደም ከኋላ በመሆን ባህላዊ ዘፈን አማክኘነት ስለ ማቿ ቤተሰቡ ጀግንነት፣ ጥንካሬ፣ ታላቅነት እና ታላቅ መሆኑን ይገልፃሉ።
ሌላው በዕለቱ ለኪሎንጋ የሚዘጋጅ የሱሪ ባህላዊ ቤት ሲሆን ሁሉም ቤተዘመድ ቤቱ ላይ በመውጣት ባህላዊ ዘፈን በመዝፈን ስለ ሟቹ እያስታወሱ ቤቱ ላይ ይጨፍራሉ ይህም ትርጓሜው ሟቹ ጥሩ ቤት እንደነበረው ማሳያ እንዲሁም በፈጣሪ ቤትም ነፍሱን እንድቀበልላቸውም ጭምር ነው።
ኪሎንጋን የሚደረግበት የተወሰነ ጊዜ ባይኖርም ሟቹ ካረፈበት የተወሰነ ጊዜ ጀምሮ በተዘመዱ እንደ አቅሙ ብዙ ዓመታት በላይም ቆይቶ ማድረግ ይችላሉ።
እንደ ሱሪ ማህበረሰብ አሁንም ይሄ ባህል እየተከናወነ መሆኑን የሚገልፁት አባቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ እንደሆነም ይናገራሉ።
በተከተል ወ/ሚካኤል
