






የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ጤና ቢሮ የጤና ኤክስቴሽን ፕሮግራም አፈፃፀምን ለማሻሻል የተዘጋጀ ስልጠና ነክ ግምገማ መድረክ ከቤንች ሸኮና ሸካ ዞኖች ለተዉጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች በሚዛን አማን ከተማ እየተሰጠ ነዉ።
መድረኩ ላይ በቅርቡ በሞት የተለዩ የክልሉ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ለሆኑ ለአቶ ተዘራ ወልደማርያም የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማድረግ ተጀምሯል፡፡
የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ ፀጋዬ ማሞ ባስተላለፉት መልዕክት በ በሀገሪቱ በማህረሰብ ደረጀ የሚሰጡ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ የጤና ኤክስቴሽን ፕሮግራም ተቀርፆ እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በርካታ ውጤታማ ተግባራት መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሆኖም ግን አሁን ላይ የጤና ኤክስቴሽን ተግባር መቀዛቀዞች እየታዩ ይገኛሉ ያሉት አቶ ፀጋዬ ማሞ ይህንን የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ውጤታማ ለማድረግ ባለሙያዎች በተሠማሩበት ተተክለው መስራት ይገባቸዋል ብለዋል ።
የጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች ተደራሽነት ፍትሃዊ ያለመሆን በፕሮግራሙ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቅሰው በአግባቡ መፈተሽ ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል ፡፡
የጤና ኬላ እና ጤና ኤክስቴንሽንን በማጠናከርና በመድሀኒት አስተዳደር ላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በተገቢው ማሳተፍ እንደሚገባም ጭምር አቶ ፀጋዬ ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ውጤታማ ለማድረግ የሚሰሩ ተግባራትን ፓርቲዉና እና መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በንግግራቸዉ በሀገራችን የጤና ኤክሰቴንሽን ፕሮግራም ተቀርፆ የህብረተሰቡን የጤና አጠባበቅ ንቃተ ህሊና በማሳደግ በዚህም ውጤታማ ስራ መሠራቱን ገልፀዋል፡፡
የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም መተግበር ከጀመረ ከ1997 ዓ.ም ወዲህ ማህበረሰቡን በማሳተፍ በሽታን ከመከላከልና መቆጣጠር ረገድ ውጤታማ የሆኑ ለውጦች መመዝገባቸዉን ተናግረዋል፡፡
የእናቶችና ህፃናት ሞት ከመቀነስ አንፃር ትርጉም ያለው ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ያሉት አቶ ኢብራሂም በፕሮግራሙ የተገኙ ስኬቶችን ማስቀጠል እንደሚገባም ገልፀዋል ።
በሀገራችን የተያዘዉን የጤና ልማት ዕቅድ በማሳካት የህዝቡን የህክምና አገልግሎት ጥያቄዎችን ለመመለስ ሁሉን አቀፍ አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ለቀጣይ 15 ዓመት የሚቆይ የጤና ኤክስቴሽን ፕሮግራም ፍኖተ ካርታ ጉልህ አስተዋፅኦ ያለዉ ነዉ ብለዋል።
በክልሉ ያለዉ የጤና ኤክስቴሽን ስራ በመቀዛቀዝእና ከፕሮግራሙ ማሻሻያ የሚጠበቁ ዉጤቶችን ማስመዝገብ ባለመቻላችን አሁን ላይ በወረርሽኝ መልኩ እየታዩ ያሉ የወባ፣የኩፍኝ በሽታዎች ስጋቶች ብቻ ሳይሆኑ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸዉን አቶ ኢብራሂም ተማም ጠቁመዋል።
በጤና ተቋማት የነፍሰጡር እናቶች ማቆያ ማሻሻልና ጥራቱን ማስጠበቅ፣ ከጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች የሚጠበቁ ተግባራት መከናወን ፣የጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች የመኖሪያ ቤት ችግሮች ፣ሞደል የሆኑ ቀበሌያትን ከመፍጠር አንፃር የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት በጤና ጣቢያ የሚሰጡ አገልግሎቶች ውጤታማ ለማድረግ ሰፊ ተግባር መከናወን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣች ንግግር ያደረጉት የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን በሀገራችን ከፍተኛ የሆነ የጤና ኤክስቴንሽን ችግር ያለበት በመሆኑ መንግሥት የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርጾ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡
ፕሮግራሙ መከላከልን መሠረት ያደረገ የጤና ፕሮግራም ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ ካፍቲን ይህንን ለማሳካት በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡
የንቅናቄ ሰነዱ የቢሮዉ የበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በዶ/ር እንዳለ ሳህሌ እየቀረበ ይገኛል።
በተከተል ወ/ሚካኤል
