
በአማራ ክልል የተጀመረው ህግ የማስከበር ስራ ውጤታማነቱን ጠብቆ እንደቀጠለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱላ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል በተወሰዱ ህግ የማስከበር እርምጃዎች ክልሉ ከሞላ ጎደል ወደ ተሟላ ሰላም እና መረጋጋት በመምጣት ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የክልሉ የጸጥታ ኃይል እራሱን እንደገና በማደራጀት የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ አበክሮ እየሰራ እንሚገኝም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በሀሰተኛ እና አደናጋሪ መረጃዎች “ከጽንፈኛ እና ዘራፊው” ኃይል ጎን ተሰልፈው የነበሩ ከ12 ሺህ በላይ ሰዎቸ በመንግስት የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የተሀድሶ ስልጠና በመውሰድ ከህብረተሰቡ ጋር መቀላቀላቸውን ዶክተር ለገሰ ቱሉ ጠቁመዋል፡፡
“በልዩ ልዩ ምክንያቶች አኩርፈው እና ተበትነው የነበሩ” ከ10 ሺ የማያንሱ የቀድሞ የልዩ ኃይል አባላትም በተመሳሳይ የሰላም ጥሪውን በመቀበል ክልሉን ከጥፋት ኃይሎች ለመታደግ የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣት ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
ቡድኑ የሚወሰድበትን እርምጃ መቋቋም አቅቶት ወደ ዘረፋ ተግባር ከመሰማራቱም በላይ መንገድ በመዝጋት የግብርና ግብአቶች ለአርሶ አደሩ እንዳይደርሱ እንቅፋት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
መንግስት በአንድ በኩል የአማራ ክልል ህዝብ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እየመለሰ በሌላ በኩል ደግሞ ሰላምን ለማጽናት እርብርብ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በተደጋጋሚ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ባልተቀበለው የሸኔ ቡድን ላይ የሚወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉንም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
በመጋቢት ወር ቡድኑ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የመከላከያ ሰራዊት ባደረገው መጠነ ሰፊ አሰሳ እና ዘመቻ በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውን እንዲሁም በሽብር ቡድኑ ተይዘው የነበሩ የማሰልጠኛ እና የሎጀስቲክስ ቦታዎች በቁጥጥጥር ስር መዋላቸውን አመላክተዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
