

የየኪ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ከሸካ ዞን ጤና መምሪያ እና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ጋር በጋራ በተሰራው ስራ ህገ ወጥ የግል የጤና ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የየኪ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ግብአት ጥራትና ቁጥጥር ስራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አስማማው አለሙ ገልጸዋል።
የስራ ሂደት አስተባባሪው ጽህፈት ቤታቸው ከሸካ ዞን ጤና መምሪያ እና ከክልሉ ጤና ቢሮ ግብአት ጥራት ቁጥጥር ጋር በመቀናጀት በሸካ ዞን የኪ ወረዳ ድንገተኛ ፍተሻ ከተደረገባቸው 12/አስራ ሁለት/የግል ጤና ተቋማት ውስጥ መያዝ የሌለባቸው ከደረጃ በላይ የሆኑ፣የመጠቀሚያ ጊዚያቸው ያለፈባቸው፣ በኢትዮጵያ ምግብ መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የመድሃኒት ዝርዝር ውስጥ የሌሉ መድሃኒቶች ጭምር በመገኘታቸው እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደተቻለ ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ግምታዊ ዋጋቸው ከ200,000/ሁለት መቶ ሺህ ብር/ በላይ የሆኑ ግብአቶችን በቁጥጥር ስር በማዋል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማስወገድ ስራ መስራቱን ተናግረዋል።
የደቡብ ምዕራብ ጤና ቢሮ ግብአት ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የጤናና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት የሆኑት አቶ አብዱልአዚዝ ፈረጃ እንደገለጹት እንደ ክልል በቁጥጥር ዘርፍ ለህብረተሰቡ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ከወረዳ እስከ ክልል ባሉን መዋቅሮች ቁጥጥርን አጠናክረን በመቀጠል በስታንዳርዱ መሰረት ሁሉም የጤና ተቋማት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የሸካ ዞን ጤና መምሪያ የግብአት ጥራት ቁጥጥር ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሀይሌ አረንጎ እንደገለጹት በቁጥጥሩ ወቅት ተቋማቱ ውስጥ የታደሰ የሙያ ፈቃድ ሳይኖራቸው የጤና አገልግሎት እየሰጡ መገኘታቸው ገልጸው ሁሉም የግል ጤና ተቋማት ህጋዊ አሰራርን በመከተል ህብረተሰባቸውን ሊያገለግሉ ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም ህብረተሰቡ የሚታዘዝለት መድሃኒት ላይ ጥንቃቄ ሊያደርግና ህገ ወጥ አጠራጣሪ ነገር ሲያጋጥም በየደረጃው ለሚገኝ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ጥቆማ ማድረግ እንደሚገባአቶ አስማማው አሳስበዋል ሲል የየኪ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘግቧል።
