የምዕራብ ኦሞ ዞን ውብ ምድር

Spread the love

የምዕራብ ኦሞ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከሚገኙ ዞኖች አንዱ ነው።

ዞኑ የሜኤን፣የዲዚ፣የሱሪና ዚልማም ብሔረሰቦች እና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን አብረው ተዋደው፣ተጋብተው፣ተዋልደው፣ሀብት አፍርተው በፍቅር የሚኖሩበት አካባቢ ነው።

የምዕራብ ኦሞ ዞን በሰብል አብቃይነቱ ፣ በወርቅና በሌሎች የከበሩ ማዕድናት ከመገለጫዎቹ ዋናዎቹ ናቸው።

ዞኑ በርካታ የውጭ ሀገራትን ቀልብ የሚስቡ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች የሚገኙበት ዞንም ነው።

በዚሁ ምዕራብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ወረዳዎች ምን እንደሚመስሉ በጥቂቱ እንመልከት።የማጂ ቱም ከተማ ከበርካታ የሀገራችን ከተሞች በዕድሜ ታላቅ ስትሆን አሁን ላይ ምን አይነት ገጽታ እንዳላት በስሱ እናስቃኛችሁ።

አንጋፋዋና ዕድሜ ጠገቧ ማጂ ከአዲስ አበባ የአምስት ዓመታት የታላቅነት የዕድሜ ባለጸጋ ናት ።

የማጂ ምድር የበርካታ ተፈጥሮ ስጦታዎች ባለጸጋ ስትሆን የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ አብራክም ነች።

በዚሁ ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ብርቅዬ የዱር እንስሳ/ውድንቢ/ መገኛም እንደሆነች ይነገርላታል።

ማጂ የኮሉ ወርቅ መፍለቂያ ፣የአኩ ፏፏቴ መገኛ፣ሚስጥራዊ ሚሺን ዋሻ ባለቤት፣የእንግሊዝ ቆንስላ ጽ/ቤት መገኛ፣የተፈጥሮ ፍል ውሃዎች እና ሌሎች የምድራችን ገጸበረከቶች የተቸሯት ምድር ነች።

ማጂ ከምትታወቅባቸው የኮልቡ ደን፣ዕድሜ ጠገብ ዕጽዋቶች፣የውርግ ደኖች፣አስደማሚ ባህላዊ እሴቶች፣ ትላልቅ ወንዞች፣የሳይ ፍል ውሃ ፣ዋሻዎች፣የእንስሳት ዱካ በተነጠፈ ድንጋይ የታተመበት፣የድንጋይ ከሰል ማዕድን ያለበት፣ለልማትና ለኢንቨስትመንት ምቹ የአየር ጸባይና የመሬት አቀማመጥ እንዲሁም ሌሎች ገጸበረከቶችን በጉያዋ አቅፋ የያዘች አልሚ ባለሀብቶችን የምትጣራ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ ናት።

ማጂ የዕድሜዋን ያህል ያልለማች፣በርካታ የታሪክ ባለቤት የሆነች ፣ እንግዳ ተቀባይ ስስት የሌለባት ከምድሯ የረገጠ የሚከብርባት የምዕራብ ኦሞ ዞን አንዷ ከተማ ናት።

በዙሪያዋ ባሉ ሳይ፣አዲካስ፣ቱምና ዙሪያዋ ቀበሌዎች የወርቅ ማዕድናትና የኦሞ ተፋሰስን ይዞ የብረት ማዕድናት የሚገኙበት አካባቢም ጭምር ነው።

ሌላው በማጂ ወረዳ የኦሞ ኩራዝ ሶስት የስኳር ፋብሪካ ተቋቁሞ ለሀገር ውስጥ ምርት በማቅረብ ላይ ይገኛል።

ማጂ_ ቱም ከተማ ካሳለፈቻቸው ከመቶዎች የዕድሜ ዓመታት በርካታ የኢትዮጵያ መሪዎች ምድሯን ለመርገጥ ቀዳሚው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያዩዋት ከተማ ሆናለች።

በምዕራብ ኦሞ ዞን ካሉት ወረዳዎች ሌላይኛዋ ቤሮ ስትሆን በስፋት ወርቅ በማምረት እና ለብሔራዊ ባንክ በማቅረብ የምትታወቅ አካባቢ ናት።

በወረዳው ወርቅ በስፋት እንዳለ ሁሉ ሊለማ የሚችል ሰፊ የእምነበረድ ማዕድንም እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በሌላ በኩልም የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስበው የሱሪና ዚልማሞ ወረዳዎችም ሰፋፊ የመልማት እምቅ የተፈጥሮ ጸጋዎች የተቸሯቸው አካባቢዎች ናቸው።

በወረዳዎቹ የአርብቶ አደሩን ህይወት የሚቀይሩ የቀንድ ከብቶች በስፋት የሚገኙበት፣የወርቅ ማዕድናት ያሉበት አካባቢ መሆኑም ዞኑን ለየት የሚያደርገው የተፈጥሮ ስጦታ ባለቤት ነው።

በሜኤኒት ወረዳዎች ደግሞ ሰፋፊ መልማት የሚችሉ ለኢንቨስትመንት ምቹ ስነምህዳር ያሉባቸው የአልሚ ባለሀብቶችን ቀልብ የሚስቡ መሬቶች ያሉባቸው ናቸው።

በተለይም በሰብልና በሰሊጥ ልማት በእንስሳት እርባታዎች ሊለሙ የሚችሉ ሰፋፊ የመስኖ አውታሮች የሚገኙባቸው አካባቢዎች መሆናቸውም መረጃዎች ይጠቁማሉ ።

በምዕራብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ተፈጥሮ የቸሯቸው ገጸበረከቶች እና የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ የሚስቡ ለኢንቨስትመንት ልማት አማራጭ አካባቢ ነው።

በታጠቅ አበበ
ምንጭ :_ ከተለያዩ መረጃዎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *