




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት የዉሃ፣ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ በክልሉ ባሉ ስድስት ዞኖች የአስር ከተሞች የዉሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ኘሮጀክት የጥናት ዝርዝር ዲዛይን የመጨረሻ ረቂቅ ሪፖርት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቦንጋ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የደቡብ ምዕራብ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ኮረፖሬሽን በክልሉ የሚስተዋለዉን የንጹህ መጠጥ ዉሃና የሳኒቴሽን ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ የጥናትና ዲዛይን ስራዎችን ከክልሉ ዉሃ፣ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ጋር ዉል ገብቶ ሲያከናዉን መቆየቱ ተጠቁሟል።
በመድረኩ የኮረፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ፍቅሩ ሌዊ ባስተላለፉት መልእክት፣ በክልሉ የውሃ ሽፋን ለማሳደግ እንዲቻል በስድስቱም ዞኖች ዉስጥ በሚገኙ የአስር ከተሞችን የንጹህ መmጥ ዉሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ስርዓት ለማዘመን የዲዛይን ስራ መሰራቱን ገልፀው መድረኩ የተሻለ ግብዓት ለማግኘት የሚረዳ እንደሆነም ተናግረዋል።
ከተሰሩት አስር የዲዛይንና ጥናት ስራዎች መካከል አራቱ የጥልቅ ጉድጓድ ፤ስድስቱ ደግሞ የምንጭ ማጎልበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳና የክልሉ ዉሃ፣ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው ባደረጉት ንግግር፣የክልሉን የንጹህ መጠጥ ዉሃና የሳኒቴሽን ችግር በዘላቂነት በመፍታት የክልሉን የውሃ ሽፋን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በቢሮው በርካታ የውሃ ግንባታዎች እየተከነወነ እንደሚገኝ የተናገሩት ሃላፊው በመጀመሪያ ዙር የ15 ከተሞች የዲዛይንና ጥናት ተጠናቆ ለግንባታ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው በሁለተኛ ዙር ደግሞ ከክልሉ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ኮረፖሬሽን ጋር ውል በመግባት በተሰራው የመጨረሻ ዲዛይንና ጥናት ውጤት ላይ ግምገማ መደረጉንም አስረድተዋል።
የክልሉ መንግሥት የንፁህ መጠጥ ዉሃ ችግሮችን ለመፍታት ባደረገው ጥረት ክልሉ ሲመሰረት 30 ፐርሰንት ከማይሞላ ሽፋን አሁን የክልሉን የውሃ ሽፋን 43 ፐርሰንት ለማድረስ መቻሉን የገለፁት ኢንጂነር በየነ የክልሉ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ኮረፖሬሽን ለፕሮጀክቶች ስኬታማነት የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለት አስገንዝበዋል።
በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖች በርካታ የውሃ ግንባታ ኘሮጄክቶች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው ይህም የህብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር የሚፈታ በመሆኑ ለስኬታማነቱም የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበትም አሳስበዋል።
በካሳሁን አሰፋ
