ባለፉት ስምንት የለውጥ አመታት በከተማቸው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን በሚዛን አማን ከተማ የሚገኙ አንዳንድ ነጋዴዎች ተናገሩ

Spread the love

“ለሁለንተናዊ ብልጽግና የማህበረሰቡ ሚና” በሚል ሀሳብ ከሚዛን አማን ከተማ ንግድ ማህበረሰብ ጋር የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ የተሳተፉና በተለያዩ የንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎች፤ በከተማዋ በተለይም ለውጡ ከመጣ በኋላ በርካታ የልማት ስኬቶች መመዝገባቸውን እና ተጨባጭ ለውጥ መታየቱን ነው የተናገሩት።

በተለይም በከተማዋ የአየር መንገድ ግንባታው፣ የደንቢ ሎጅ እና የኮሪደር ልማት ስራዎች የከተማዋን እድገት እያፋጠነው መሆኑን አመላክተዋል።

በከተማዋ በተለይም የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታ፣ የቆሻሻ አወጋገድ ስርአት፣ የከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ እቅርቦት እና የመብራት መቆራረጥ ችግሮች ሊቀረፉ ይገባል ብለዋል።

ከዋጋ ንረት ጋር ተያይዞም እንደሀገር ያሉ ችግሮች ቢኖሩም ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪን በመግታት የህዝቡን ቅሬታ መፍታት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ከፊታቸው የሚካሄደው ሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫ ላይ በነጻነት በመሳተፍ የሚፈልጉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የሚዛን አማን ከተማ ኢንዱስትሪ እና ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ጌታቸው መለሰ እንደተናገሩት፤ በከተማ አስተዳደሩ ከስድስት ሺ በላይ በተለያዩ የንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎች መኖራቸው ገልጸው ከእነርሱም ከ875 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል ብለዋል።

በከተማዋ ያለውን የዋጋ ንረት ለማስተካከል ህገ-ወጦችን ወደህጋዊ ከማስገባት ባለፈ የሰንበት ገበያን በማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከጅምላ ነጋዴዎች ጋር የዋጋ ገበያ ጥናት በማካሄድ ህጋዊ የዋጋ ተመን በማዘጋጀት የቁጥጥር ስራ ይሰራል ብለዋል።

የሚዛን አማን ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ሰለሞን ለዊ በበኩላቸው፤ በከተማዋ እየታየ ለመጣው ፈጣን እድገት የንግዱ ማህበረሰብ ድርሻ የጎላ ነው ብለዋል።

ነጋዴው ማህበረሰብ በከተማዋ በተካሄደው መልሶ ግንባታ እና የኮሪደር ልማት ስራዎች ቤቱን በነጻ ከማፍረስ ጀምሮ ከሀምሳ አምስት ሚሊየን ብር በላይ ለኮሪደር ልማቱ በማዋጣት በራሳቸው ወጪ መገንባት ችለዋል ብለዋል።

በከተማዋ የሚታየውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከፌደራል መንግስት ጋር እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ እና የኑሮ ውድነትን ለመከላከል የሰንበት ገበያን ከማጠናከር ባለፈ ተገቢ የቁጥጥር እና የክትትል ስራዎችን በመተግበር ዋጋ የማረጋጋት ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን መምሪያ ምክትል የመምሪያ ኃላፊ አቶ ሽመልስ መኩሪያ በበኩላቸው፤ ለከተማው ፈጣን እድገት መንግስት ከሚሰራቸው ተግባራት ባለፈ የነጋዴው ድርሻ የላቀ ነው ብለዋል።

የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ጠቁመው፤ በተለይም በከተማዋ የሚታዩ የቆሻሻ አወጋገድ ስርአቶችን እና የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ከፈታ በጣይ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የነጋዴው ማህበረሰብም በቀጣይ በሚካሄደው ሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫ ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል ሲል ደሬቴድ ሚዛን ቅርንጫፍ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *