
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ዛሬ ተፈራረሙ።
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) ሥምምነቱን ፈርመዋል።
ሥምምነቱ በሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመገንባት የሚያስችል የሚሰራበት መሆኑን ተገልጿል።
ከሥምምነቱ በኋላ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ባደረጉት ንግግር፤ ከቤተሰብ ጀምሮ በልጆችና ታዳጊዎች ላይ በመስራት ሙስናን አምርሮ የሚታገል ትውልድ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
በሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ግንባታ ላይ በማተኮር ለሀገር ልማትና እድገት ጥሩ መሰረት ማኖር አስፈላጊ መሆኑን አንስተው ለዚህም በጋራ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የመገንባት ጥረቱ እውን የሚሆነው ሙስናን የሚጠየፍና በፅኑ የሚታገል ትውልድ መገንባት ሲቻል ነው ብለዋል።
በመሆኑም በጥሩ ስብእና የተገነባ ትውልድ የመፍጠር ጥረቱ በልዩ ትኩረት የሚሰራበት መሆኑን ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
