የተረጂነትንና የጠባቂነትን አስተሳሰብ በመቀነስ በራስ አገዝ በክልሉ የሚታየውን የእርዳታ ፍላጎት ለመሸፈን መስራት ይገባል። ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

Spread the love

“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በመሸጋገር የቤተሰብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ” ያለመ ክልላዊ የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል ።

በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

በእርዳታ ያደገ ሀገርም ግለሰብም የለም ያሉ ሲሆን ይህንን ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሚያጋጥሙንን አደጋዎችን አቅማችንን በመገንባትና ህዝባችንን በማስተባባር ሊንወጣዉ ይገባልም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ

በክልሉ በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሰራሽ አደጋ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ወገኖችን በመለየት መርዳት እንደሚገባ ተናግረዋል ።

በክልሉ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልል ባለው ደረጃ በሰው ሰራሽ አደጋ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ወገኖችን በመለየት 70 ከመቶውን በራስ አቅም መርዳት የሚያስችሉ ስራዎችን መስራት ይገባል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።

በክልሉ በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦችን ፈጥኖ መርዳት እንዲያስችል ዞኖች ከወዲሁ ትኩረት በመስጠት መስራትና ምርት ማከማቸት እንደሚገባቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል ።

የሴፍትኔት ተረጂዎችን ቁጥር በመቀነስ ምንም አማራጭ የሌላቸውን በመለየት ድጋፍ የሚያገኙበትን አሰራር መዘርጋት እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናግረዋል ።

የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ በሰጡት አስተያየት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ከተረጂነት አስተሳሰብ የተላቀቀ ማህበረሰብ መፍጠር ይኖርብናል ብለዋል።

የተረጂነት አስተሳሰብ የሉዓላዊነት ጥያቄ እየሆነ በመምጣቱ ይህንን በማረም ሀገራዊ አቅማችንንና ያሉ ዕድሎችን በመጠቀም የእርዳታ ተጠቃሚ ማህበረሰብ ቁጥርን በመቀነስ ወደ ምርታማነት በመቀየር በትኩረት ሊሰራበት ይገባልም ብለዋል።

የእርስ በርስ መተጋገዝንና መረዳዳት ባህልን በማዳበር ዓለም አቀፍ የእርዳ ፍላጎቶችን በመቀነስ ሀብት የሚገኝበትን መንገድ በመቀየስ ምርታማነትን ማሳደግ አለብን ብለዋል አቶ ነጋ አበራ።

በክልሉ 23 ሺህ የሚጠጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የእርዳታ ተጠቃሚ ሲሆኑ በከተማም ሆነ በገጠር ተገቢውን መረጃ በማጣራት ትክክለኛ የእርዳታ ተጠቃሚዎችን በመለየት ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም አቶ ነጋ አበራ ገልጸዋል።

የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ዶክተር ለማ መሰለ በበኩላቸው በክልሉ የተረጂነትን ቁጥር በመቀነስና በራስ አቅም ተረጂዎችን ለመርዳት በሚደረገው የስራ እንቅስቃሴ በየዞኖቹ አጥጋቢ አለመሆኑንና ትኩረት ያልተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል ።

ይህ እንደዚህ መሆኑ ደግሞ በክልሉ አቅም 70 ከመቶ ተረጂዎችን ለመርዳት የሚደረገውን ዕቅድ የሚያስተጓጉል በመሆኑ ዞኖች ትኩረት በመስጠት ወደ ተግባር እንዲገቡ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ።

በቀጣይ በክልሉ የሚከናወኑ ተግባራትን የተመለከተ መነሻ ዕቅድ ለክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት ዶክተር ለማ መሰለ አቅርበዋል።

በውይይት መድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾን ጨምሮ የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣የዞን ዋና አስተዳዳሪዎች እና የመንግስት ዋናና ምክትል ተጠሪዎች ፣የግብርና መምሪያ ኃላፊዎች ተገኝተዋል ።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *