የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ የአንድነትና የነፃነት መገለጫ ነው፦የተከበሩ አቶ ዮሐንስ ካሳሁን

Spread the love

18ኛው ብሔራዊ የሰንደቅዓላማ ቀን በዓል በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

“ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ!” በሚል መሪ ቃል ነው በዓሉ የተከበረው።

በበዓሉ መልዕክት ያስተላለፉት የሸካ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ዮሐንስ ካሳሁን ሠንደቅ ዓላማ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ የታተመ የሀገራዊ አንድነትና ነፃነት መገለጫ ታላቅ የብሔራዊ ኩራት ዓርማ እንደሆነ አመላክተዋል።

የአንድነታችንና የሕብረታችን ማሳያ፣ ጀግኖች አያቶቻችን ወራሪዎችን በማሸነፍ ለመላው የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት የሆነውን ሠንደቅዓላማ የህይወት መስዋዕትን ከፍለው ለአዲሱ ትውልድ ማስረከባቸውን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ክብርና ተገቢውን ከፍታ አስጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሀገራዊ ሉዓላዊነትንና የግዛት አንድነትን ማስቀጠል ከአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅ ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል የተከበሩ አቶ ዮሐንስ።

የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ -ጉባኤ የተከበሩ አቶ መሰለ ከበደ በበኩላቸው የብሔራዊ ሰንደቅዓላማ ቀን መከበር ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ያለንን ቁርጠኝነት የምናድስበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ሠንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር መንግሥትና ሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ሥልጣን፣ ነፃነት፣ ዕድገትና ማሕበረሰባዊ ትስስር መገለጫ መሣሪያ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።

ሕብረ -ብሔራዊ ወንድማማችነትን በማጽናት የሀገሪቷን የዕድገት ከፍታ ማረጋገጥ እንደሚገባ ያስገነዘቡት የተከበሩ አቶ መሰለ የሰንደቅዓላማ ክብሩንና ታላቅነቱን መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ግዴታ መሆኑን አሳስበዋል።

ሰንደቅዓላማ የብሔራዊ ክብርና ኩራት መገለጫ መሆኑን በመግለፅ ለሠንደቅ ዓላማ ክብርና ተገቢውን ቦታ መስጠት እንደሚገባ የገለፁት የፓናል ውይይት ተሳታፊዎች ናቸው ።

ክብረ በዓሉ ሠንደቅ ዓላማ በመስቀል፣ ቃለ መሐላ በመፈፀም፣ በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።

በዓሉ የቴፒ ብዝሀ ማዕከል አመራሮችና የዞን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ፣ የጸጥታ አካላት፣የመንግሥት ሠራተኞችና ተማሪዎች በተገኙበት ነው የተከበረው ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *