




በኮንታ ዞን 18ኛው የሰንደቅዓላማ ቀን በዓል በተለያዩ ሁኔቶች ተከብሯል።
የዕለቱን መልዕክት ያስተላለፉት የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ ብሄራዊ የሰንደቅዓላማ ቀን በዓል ሲከበር ለሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር በመስጠት ዜጎች የጋራ ዕሴቶቻቸውን እንዲያጠናክሩና ሀገራዊ አንድነትና መግባባትን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ገልፀዋል።
ሰንደቅ ዓላማ ዜጎች ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር የሚያሳዩበትና የማንነታቸው መገለጫ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያዊያን ጽኑ ተጋድሎ የቆመ በዓለም ተምሳሌት የሆነ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያን ተምሳሌት በማድረግ ሰንደቅ ዓላማቸውን ከኢትዮጵያ ጋር ያመሳሰሉበት የማንነትና የድል ማሳያ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
በሰንደቅ ዓላማ ስር ሆነን ሀገራዊ መግባባትና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ማፅናትን ያስፈልጋል ያሉት አቶ ታከለ ለሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር በመስጠትና ይህንን የሀገር ፍቅር ስሜት ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ኃላፊነት ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።
የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ብርሃኑ አቱሞ በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ 863/2006 አንቀጽ 2 መሠረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ዕለተ ሰኞ የሚከበረው የሰንደቅዓላማ ቀን በዓል ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ “ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብስራት፣ ለብሄራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ህዳሴ” በሚል መሪ ቃል በመላው ኢትዮጵያ በመከበር ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያዊያን የማንነት መገለጫና ዓርማ ነው ያሉት ዋና አፈ ጉባኤው ኢትዮጵያዊያን ሰንደቅ ዓላማቸውን በመያዝና ከፍ በማድረግ በየዘመናት የገጠማቸውን ፈተና በድል በማለፍ፣ ሀገራዊ ጀብድና አርበኝነት የፈፀሙበት መሆኑን አስረድተዋል።
በበዓሉ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ፣ የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ብርሃኑ አቱሞን ጨምሮ የዞኑ የመንግስትና የፓርቲ ስራ ኃላፊዎች የፀጥታ አካላት፣ መንግስት ሰራተኞችና ሌሎች ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን በዓሉ በፖሊሳዊ ትርዒት እና በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል ሲል የዘገበው የኮንታ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።
