
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ የካፌቾ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው “ማሽቃሮ” የይቅርታ፣ የፍቅርና የማህበራዊ ትስስር ተምሳሌት መሆኑን ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዓሉን አስመልክተው ለመላው የካፌቾ፣የናኢና የጻራ ብሔር ተወላጆች ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፣ ማሽቃሮ ከቀን መቁጠሪያነት የዘለለ ጥልቅ ታሪካዊና ባህላዊ ፋይዳ ያለው የማንነት መገለጫ በዓል መሆኑን አስምረውበታል።
ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ በመልዕክታቸው እንዳመለከቱት፣ የማሽቃሮ በዓል ማህበረሰቡ ያለፈውን ዓመት ገምግሞ ለተገኙ ስኬቶች ፈጣሪን የሚያመሰግንበትና ለአዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ ሰንቆ ለላቀ ስራ የሚነሳሳበት ልዩ የሽግግር ወቅት ነው ብለዋል፡፡
“ማሽቃሮ ቂምና ጥላቻን አስወግደን ይቅር የምንባባልበት፣ የተራራቁትን አቅርበን ፍቅር የምናድስበት፣ የቤተሰብ ትስስርን አጠናክረን አንድነታችንን የምናጸናበት ውድ የማህበራዊ እሴታችን ማሳያ ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በዓሉ ታሪክንና ባህልን ለቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር ወርቃማ ድልድይ መሆኑን አብራርተዋል።
በመጨረሻም ርዕሰ መስተዳድሩ ህዝቡ በዓሉን ሲያከብር ታላላቅ እሴቶችን በማጎልበት፣ ሰላምን በመጠበቅና ለጋራ ልማት በጋራ በመቆም እንዲሆን ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
አዲሱ የ”ማሽቃሮ” ዘመን የሰላም፣ የፍቅር፣ የጤናና የብልጽግና እንዲሆን ያላቸውን ልባዊ ምኞት ገልጸዋል።
