















በክልሉ የግሉ ዘርፍ የኢንቨስትመንት ተሳትፎን ለማሳደግ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው፦ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ
የኢንቨስትመንት ዘርፍ ዕድገትና ልማትን በማፋጠን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እና የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያለውን ፀጋና እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም ተጠቅሞ ባለው አቅም ልክ ዘርፉ ለክልሉ ልማትና ዕድገት አስትዋጽኦ እንዲያበረክት በማስቻል፤ በክልሉ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዘገብ የክልሉ መንግስት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከበደ ተስፋዬ፤ ክልሉን ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ምቹ በማድረግ ባሉት ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች መሰማራት የሚፈልጉ አልሚዎችን በመሳብ ለዘርፉ ውጤታማነት ርብርብ በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቢሮው ተገቢውን መስፈርት ላሟሉ ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ከመስጠት ባለፈ የፕሮጀክቶችን እንቅስቃሴ በመከታተል እና ከአልሚዎች ጋር በቅርበት በመስራት ለዘርፉ ውጤታማነት ያለውን ቁርጠኛነት በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
ክልሉ እምቅ አቅም ያለው በመሆኑና ይህንን ወደ ውጤት በመቀየር የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማጎልበት በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በየዓመቱ የአልሚ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል ብለዋል አቶ ከበደ።
በዚህ የግሉ ዘርፍ የኢንቨስትመንት ተሳትፎን ለማሳደግ በተሰራው ስራ ወደ ክልሉ በርካታ ባለሀብቶች መጥተው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው እያለሙ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በ2017 የበጀት አመት ከ14 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 114 ባለሀብቶች በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ መሠማራታቸውና 18 ሺህ 244 ሄክታር መሬት ለአልሚ ባለሀብቶቹ መሰጠቱንም ኃላፊው አብራርተዋል።
በአሁኑ ሰዓት በክልሉ 1ሺህ 60 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ከበደ ክልሉ ከተመሰረተ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ 405 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን አብራርተዋል፡፡
እነዚህም ፕሮጀክቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ወደ ስራ የገቡ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው በግብርናው ዘርፍ 546፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ 326 እና በአገልግሎት ዘርፍ 124 ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ 1ሺህ 60 ፕሮጀክቶች በክልላችን እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
ወደ ስራ ከገቡት አልሚ ባለሀብቶች መካከልም በግብርና ዘርፍ የተሰማሩት ከ57 በመቶ በመውሰድ አብላጫውን ድርሻ መያዛቸውን የተናገሩት አቶ ከበደ ከስራ ዕድል ፈጠራ አኳያም በክልሉ ወደ ስራ የገቡት ፕሮጀክቶች በቋሚነት እና በጊዜያዊነት ከ95 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን አስረድተዋል።
በክልሉ በስራ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶቹ የሚፈለገውን ውጤት ከማስመዝገብ አንፃር ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ያነሱት ኃላፊው በቢሮው በኩል የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከመሬት ፖቴንሻል ጥናት እና መሰል ውስንነቶችን በመቅረፍ የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በዓመታዊ ሰብል ላይ እየሰሩ ያሉ ባለሀብቶች የግብዓት፣ የቴክኖሎጂ፣ የምርጥ ዘር አጠቃቀም እና የአስተራረስ ዘዴዎች ላይ ክፍተት መኖሩን የጠቀሱት ኃላፊው በቀጣይም ለአካባቢው ማህበረሰብ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማስፋት፣ የኑሮ ውድነት ቅነሳ እና ስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡
አልሚ ባለሀብቱ በገባው ውል መሠረት ቶሎ ወደ ስራ እንዲገባ ድጋፍና ክትትል ሲደረግ መቆየቱን ያወሱት አቶ ከበደ እንደ ክልል በባለፈው 2017 በጀት ዓመት በኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ በተደረገው ቁጥጥርና ኦዲት እንዲሁም በተወሰደው ህጋዊ እርምጃ የ37 ፕሮጀክቶች መሬት መነጠቃቸውን፣ 25 ከፕሮጀክቶች ቅነሳ መደረጉንና ለ36 ፕሮጀክቶች ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በኢንቨስትመንት ስም መሬት ወስደው በትክክል ሳያለሙ ከቆዩ ባለሀብቶች እጅ ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተቀንሶ ወደ መሬት ባንክ ገቢ እንዲደረግ በማድረግ እርምጃ መወሰዱን የገለጹት ኃላፊው ይህ የክትትል፣ ኦዲትና እርምጃ የመውሰድ ሥራ አሁንም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አስረድተዋል።
በክልሉ በኢቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ቢሮው ከባለሀብቱና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ኃላፊ በተያዘው 2018 በጀት አመት ከ160 በላይ ባለሀብቶችን በግብርና፣ በአገልግሎት እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ለማሰማራት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ወደ ክልሉ መጥተው ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሀብቶች ከ145 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተለይቶ የተዘጋጀ መኖሩን የተናገሩት አቶ ከበደ በኢንዱስትሪ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ አልሚዎች ይበልጥ እንደሚበረታቱ ጠቁመው ባለሀብቶች በክልሉ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም መጥተው እንዲያለሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በተከተል ወ/ሚካኤል
