የሸኮ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫና የምስጋና በዓል የክልሉን ህዝቦች ትስስር የተጠናከረበት ኢትዮጵያዊነትን በተግባር ያሳየ በዓል ነው- ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

Spread the love

የሸኮ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫና የምስጋና በዓል “ቲካሻ ቤንጊ” በተለያዩ ባህላዊ ኩነቶች ደምቀው በሸኮ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።

በበዓሉ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፥ የሸኮ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫና የምስጋና በዓል የክልሉን ህዝቦች ትስስር የተጠናከረበት ኢትዮጵያዊነትን በተግባር ያሳየ በዓል ነው ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ የራሳቸው ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ እና የማንነት መገለጫ ያላቸው ህዝቦች ተዋደው በአንድነት የሚኖሩበት እንደኾነ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድር፥ ቲካሻ ቤንጊ ከእነዚህ ድንቅ የማኅበረሰብ ሀብቶች አንዱ ነው ብለዋል።

በዚህ ድንቅ የማኅበረሰብ ባህላዊ ሀብት የሾኮ ብሔር ተወላጆች ካሉበት ወደ ቀያቸው በመሰባሰብ በታላላቆች ምክር፣ ታናናሾችን በመመረቅ እና በባህላዊ አልባሳት ደምቀው በተለያዩ ክዋኔዎች የሚከበር በዓል ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

ሸኮ ከድንቅ ተፈጥሮ ሀብት በተጨማሪ የዳበረ የማኅበረሰብ የግጭት አፈታት ባህል ያለው ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ይህንን አኩሪ የማኅበረሰብ ዕሴት በማጉላት ለህዝቦች ሁለንተናዊ ለውጥ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ይህንኑን የህዝቦች አንድነትና መሰባሰብ ለዘላቂ የሠላም ግንባታ ማዋል ይገባል ያሉት ዶክተር ነጋሽ፥ ወጣቶች የበዓሉን ዕሴት በተገቢው በመረዳት የታየውን ወንድማማችነትና አንድነት የማጠናከር ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ከፍቴን በበኩላቸው የዘርፉ ምሁራን የበዓሉን ታሪክ በመሰነድ፣ በጥናትና ምርምር ማዳበር እንደሚገባ በማሳሰብ የዞኑ መንግሥት በዓሉን በመጠበቅና በማልማት ለትውልድ ለማስተላለፍ ይሰራል ብለዋል።

በዓሉ ለረዥም ዓመታት መከበር ካቆመበት ዳግም መከበር ከጀመረ ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ መኾኑን የገለጹት የሸኮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሪ ጉሩሙ፥ ይህም የብልጽግና ፓርቲ ለህዝቦች የወል እውነት የሰጠው እውቅና መኾኑን ተናግረዋል።

በዓሉን በማልማትና በስፋት በማስተዋወቅ ቀጣይ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የወረዳው መንግሥት በትኩረት እንደሚሰራ ያስታወቁት አቶ አሪ፥ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ መጠናከር አለበት ብለዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *