
በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን የክልሉን የዘጠኝ ወራት የፓርቲ የሥራ አፈጻጸም እና 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሥራዎች አስመልክቶ ለሚዲያዎች መግለጫ ሰጥተዋል።
ኃላፊው በመግለጫቸው፤ በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በፓርቲና መንግሥት የተመሩ የንቅናቄ አጀንዳዎች በተሳካ ሁኔታ መፈጸማቸውን ገልጸዋል።
በፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ለአመራሮችና ለአባላት በየጊዜው የሚሰጡ ስልጠናዎች የአመለካከትና የተግባር አንድነት በመፍጠሩ ውጤቶች እንዲመዘገቡ እያስቻለ ነው ብለዋል።
በክልሉ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን ለመፍታት የአዝማሚያ ግምገማዎች በማካሄድ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕዝቡ የሚያነሳቸው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዲፈቱ የአሰራር ሥርዓቶች ማሳለጥና ብልሹ አሰራሮች መቅረፍ እንዲቻል ሰፊ ተግባራት ተከናውኗል።
በተለይም የክልሉ “የሚዛን መሶብ አንድ ማዕከል” አገልግከበደ መጀመሩ የህብረተሰቡ እርካታ እንዲጨምር አድርጓል ያሉት አቶ ፍቅሬ፤ አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ በመሆኑ ግልፅነትን እና ተጠያቂነትን እያሰፈነ ነው ብለዋል።
በቦንጋ፣ ሚዛን አማን፣ ቴፒ፣ ታርጫ እና አመያ ከተሞች ተመሳሳይ መሶብ አንድ ማዕከላት እየተገነቡ ሲሆን በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ገልጸዋል።
በዘጠኝ ወራት ከ16 ሺህ በላይ የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ወደ ራስ አገዝ አቅም መግባታቸውን ጠቁመው፣ ቀሪዎቹንም በቅርቡ በማስመረቅ ተረጂነትን ዜሮ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአደጋ ጊዜ ዝግጅትን ለማጠናከር የእርሻ ስራዎችን ማስፋፋት፣ ምርት ማከማቸት እና መጋዘን መገንባት ላይ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል አቶ ፍቅሬ አማን።
በዚህም ከ211 በላይ የምርት ማከማቻ መጋዘኖች አዳዲስ ተገንብተውና የነበሩት ተጠግነዉ ወደ ሥራ ገብቷል ነው ያሉት።
በጋ ስንዴ እና “ሌማት ትሩፋት” ኢንሼቲቭ በትኩረት መከናወኑ በቤተሰብ ደረጃ የኢኮኖሚ ብልጽግና እንዲረጋገጥ እየረዳ መሆኑን ኃላፊው ጠቅሰዋል።
የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ኬላዎችን በማስወገድ ነጻ የምርት ዝውውር እንዲኖር መደረጉን ገልጸዉ በከተሞች የሰንበት ገበያዎች በማቋቋም ሕብረተሰቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ፓርቲዉ ለአቅመ ደካሞች የቤት ግንባታ እና የራስ እገዛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በክልሉ “አንድ ወረዳ አንድ የገጠር ሞዴል መንደር” ፕሮግራም ስር ከ145 በላይ ቤቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
900 ሺህ የሚጠጉ የክልሉ ነዋሪዎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እንዲይዙ መደረጉን ገልጸው፣ “አምስት ሚሊዮን ኢትዮ ኮደርስ” ስልጠና ላይም እየተሰራ ቢሆንም አሁንም ትኩረት መስጠትን ይፈልጋል ብለዋል።
ኃላፊው ያለ ተቋም ግንባታ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት እንደማይታሰብ በመግለጽ፣ በክልሉ በሶስት ዞኖችና በ10 ወረዳዎች 13 የፓርቲ ጽ/ቤት ህንጻዎች እየተገነቡ እንዳሉ ተናግረዋል።
የሴቶችና ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጠናከር የተደራጀ ሥራ እየተሰራ ሲሆን፣ በሀገር ግንባታ ያላቸውን ሚና እንዲያሳድጉ ትኩረት መሰጠቱንም እንዲሁ።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ዝግጅቶች እየተጠናከሩ መሆኑን ገልጸው፣ የመራጮች ምዝገባ መጠናቀቁንም አስታውቀዋል።
የምርጫ ቅስቀሳ ሥራዎችም በሁሉም መዋቅሮች እየተካሄዱ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ፍቅሬ አማን፤ የክልሉ ሕዝብ ግንቦት 24 በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ተሳትፎአቸውን እንዲያጠናክሩ አመልክተዋል።
በክልሉ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለው አብሮ የመስራት ትብብር ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ የጋራ የሥራ ባህል እንዲጠናከርም ጥሪ አቀርበዋል።
አቶ ፍቅሬ አማን በመጨረሻም የክልሉ ሕዝብ እስካሁን በሰላምና በልማት ላይ ያሳየውን ተሳትፎ በቀጣይነትም አጠናክረዉ እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በፍቅር ከበደ
