







የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ፋይናንስ ቢሮ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የ3ኛ ዙር የጋራ ምክክር መድረክ በሚዛን ከተማ አካሂዷል ።
በምክክር መድረኩ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅች በኩል የተከናወኑ የስራ አፈጻጸም ረፖርት ቀርበው ከተሳታፊዎች ሀሳቢና አስተያየት ተነስተው ውይይት ተደርጎበታል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ መቱ አኩ እንደተናገሩት ድርጅቶች በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች ፕሮግራም በመቅረጽ የሚያከናውኑትን ተግባር እንዲያጠናክሩ አስገንዝበዋል።
በክልሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚያከናውናቸው ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ አሰፈላጊው የድጋፍና ክትትል ስራዎችን እንደሚጠናክሩ ያስታወቁት የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ ናቸው።
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በርካታ ሀብት በማፍሰስ ህዝብን የሚጠቅሙ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርጸው በተቀመጠው አዋጅና ደንብ መሰረት ውል በመፈራረም ወደ ስራ በመግባት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።
ኃላፊዋ ድርጅቶቹ በግብርና፤በጤና፤በውሃ ልማት፤በሴቶችና ህጻናት፤በትምህርትና መሰል ዘርፎች የጀመራቸውን ተግባራት እንዲያጎልብቱ የክልሉ መንግስት በመቀናጀትና በመናበብ ይሰራልም ብለዋል።
በዚሁም የልማት ፕሮጀክቶች የፍትሃዊ ተደራሽነት እንዲኖር ፕሮጀክት ስርጭት ከማድረግ አስቀድሞ በየአከባቢ ያለው አንገብጋቢ የልማት ጥያቄ መነሻ ተደርጎ የስርጭት ስራዎች እንደሚከናወኑም ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክልሉ ያለው ሰፊ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የህዝቡ የመልማት ፍላጎት ለመሙላት መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች በሰፊው ወደ አከባቢው እንዲገቡ ትኩረት እንዲሰጥም ጠይቀዋል።
በዚህም የአሰራርና፣የድጋፍ እንዲሁም ክትትል ላይ የሚስተዋለው ጉድሌቶች እንዲታረሙም ተነስቷል።
በመጨረሻም ለመድረኩ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋጾኦ ላበረከቱ ድርጅቶች የምስጋና ሠርተፍኬት በማበርከት እንዲሁም የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የጋራ ባለሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት መድረኩ ተጠናቋል።
በፍቅር ከበደ
