በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ታዋቂ ሰዎች አጀንዳ የማሰባሰብ ውይይት ዛሬም ቀጥሏል።

Spread the love

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ታዋቂ ሰዎች ጋር አጀንዳ የማሰባሰብ ውይይት ተጀምሯል።

ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ የተሰባሰቡ ታዋቂ ሰዎች በአካባቢያቸው ህዝብን በማስተባበር ብዙ መስራት የቻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በሚኖረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ውይይት ላይ የምታፈልቁት ሀሳብ በግብታዊ ሳይሆን መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መሆን እንዳለበት ኮሚሽነር ዘገዬ አሳስበዋል ።

ሀገሪ ያለችበትን ችግር መፍታት የሚቻለውም ትልቁ ትንሹን በማክበር ፣ትንሹ ለትልቁ በመታዘዝ በማክበርና በመወያየት እንጂ የጠመንጃ አፈሙዝ በማዞር አይደለም ብለዋል ኮሚሽነሩ።

ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ በበኩላቸው በሀገሪቱ አለመግባባቶች መኖራቸው ግጭቶችና መገፋፋቶች እየፈጠረ በመሆኑ አካታችና ሰፋፉ ህዝባዊ መድረኮችን በማመቻቸት ከህዝቡ የተገኘውን ምክረ ሀሳብ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ መፍትሔ ማፈላለግ የኮሚሽኑ ዋና ተግባር መሆኑን ተናግረዋል ።

በውይይቱ በሀገሪቱ ያለውን የፖለቲካ፣የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲቀረፉ ታዋቂ ሰዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸውም ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ጠይቀዋል ።

የታዋቂ ሰዎች አጀንዳ የማሰባሰብ ውይይቱ በቡድን ቀጥሎ እየተከናወነ ሲሆን በሀገራዊ ምክክር መድረክ የሚሳተፉትንም የሚመርጡበት እንደሆነም ተገልጿል ።

በነገው እለት እነዚህ ተሳታፊዎች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች ጋር በመሆን ውይይቱን እንደሚካፈሉም ተገልጿል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *