
ዶናልድ ትራምፕ ሦስት ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን ሙከራ ከማድረጋቸው በፊት በአሜሪካ ታዋቂ እና አነጋጋሪ ቢሊየነር እንዲሁም በቴሌቭዥን መስኮት የማይጠፉ ዝነኛና አለፍ ሲሉም አስገራሚ ፖለቲከኛ ስለመሆናቸው ይነገራል።
(Make American great again) አሜሪካንን መልሶ ታላቅ ማድረግ በሚለው መለያቸው በአውሮፓውያኑ 2016 ምርጫ ብቅ ያሉት ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ሆነው ነበረ ከዲሞክራቷ ሂላሪ ክሊንተን ጋር የተፎካከሩት።
በ2016 የምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት የጎረቤት ሀገር ሜክሲኮ የዕፅ አዘዋዋሪዎችን ስራ ለአሜሪካ አስጊ መሆኑን በማንሳት በሁለቱ አገራት መካከል አጥር ለመገንባት እንዳቀዱ እና ወጪውንም ሜክሲኮ እንድትሸፍነው እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው ተፎካክረዋል።
ተፎካክረው ብቻ አላበቁም አወዛጋቢ የሆኑ ምላሾችን በመስጠትና ተቀናቃኞቻቸውን ባገኟቸው መድረክ ሁሉ ዝም በማሰኘት የሚታወቁት ዶናልድ ትራምፕ ሂላሪ ክሊንተንን አሸንፈው የአሜሪካ 45ተኛው ፕሬዚዳንት ሆኑ።
ከ2016- 2020 በዘለቀው የአራት ዓመታት የስልጣን ዘመናቸው አሜሪካን ከአየር ንብረት ለውጥ እና ከንግድ ስምምነቶች እንድተወጣ አድርገዋል።
በብዙ ሀገራት ዜጎች ጥርስ እንዳስነከሰባቸው የሚነገረው ከሰባት የሙስሊም አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይመጡ ማገዳቸው ሌላው ትልቅ የሚባል ውሳኔ ነበረ።
ትራምፕ በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ ሥልጣን ላይ ሳሉ የተከሰሱ ሦስተኛው ሰው ሲሆኑ ይህ ብቻ ሳይሆን በ2024ቱ ምርጫ በመወዳደር ላይ እያሉ ጥፋተኛ በመባል የገንዘብ ቅጣት የተፈረደባቸው የመጀመርያው የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ናቸው።
አራት አስገራሚ የስልጣን አመታትን ያሳለፉትና በሚፅፏቸው የማህበራዊ ሚዲያ ሀሳቦች አወዛጋቢ ፕሬዚዳንት ስለመሆናቸው የሚነገርላቸው ትራምፕ በ2020 የአሜሪካ ምርጫ ቢወዳደሩም በአዛውንቱ ባይደን ተሸንፈው ከኋይትሀውስ ወጥተዋል።
እኝህ አነጋጋሪ ፕሬዚዳንት በጆ ባይደን የተሸነፉበትን መንገድ ተጭበርብሯል ብለው እንደሚያምኑ በጊዜው ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ወደ ንግዱ ዓለም በድጋሚ ይሰማራሉ የተባሉት ትራምፕ ግን ከአራት አመታት ጥበቃ በኋላ በ2024ቱ የአሜሪካ ምርጫ አሜሪካን ድጋሚ ሀያል አደርጋታለሁ በማለት ተፎካካሪ ሁነው ተገኙ።
በአሜሪካ ምድር የሚታወቁት ባለሀብት እና የሪል ስቴት ንግድ ባለቤት ፍሬድ ትራምፕ አራተኛ ልጅ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ በዚህኛው ምርጫ ከካማላ ሀሪስ ጋር ብርቱ ፉክክር አድርገዋል።
አስገራሚው ነገር ትራምፕ በ2024ቱ የአሜሪካ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ለመሆን የተወዳደሩት በአራት የተለያዩ የክስ መዝገቦች 91 ክሶች ቀርቦባቸው እያለ መሆኑ ነው።
በምርጫ ቅስቀሳ ላይ ሳሉ የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ትራምፕ በጥይት ተጨርፏል የተባለ ጆሯቸውን አሽገው “መቼም ተስፋ አንቆርጥም በማለት” ነበረ ፓርቲያቸው በይፋ ዕጩ አድርጎ በሰየማቸው መድረክ ላይ ተገኝተው ብዙዎችን ያስገረሙት።
በምርጫ ፉክክሩ ወቅት ያቀረቧቸው ፖሊሲዎች በተለይም በህገወጥ ስደተኞች ላይ የሚስተዋልባቸው ንዴት እና መግፋት “ከእኛ ቁጥር በላይ እነሱ ሀገራችንን ተቆጣጥረዋል” ሲሉ መግለፃቸው እና የዩክሬን ሩስያን ጦርነት ለማስቆም እጠቅማለሁ ማለታቸው አለምን ለሁለት ከፍሎ በከፍተኛ ሁኔታ አነጋግሯል።
46ተኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩትን ጆ ባይደንን “አርጅተሀል፤ ለፕሬዚዳንትነት አትሆንም” የዲሞክራቶችን እጩ ካማላ ሀሪስን ደግሞ “ከእኔ የተሻልሽ አይደለሽም” ያሉት ዶናልድ ትራምፕ አስገራሚ ፉክክር በታየበት በ2024ቱ የአሜሪካ ምርጫ ካማላ ሀሪስን አሸንፈው የልዕለ ሀያሏ ሀገር አሜሪካ 47ተኛው ፕሬዚዳንት ለመሆን በቅተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ስልጣን ከያዙት ከግሮቨር ክሊቭላንድ ቀጥሎ ተከታታይ ያልሆኑትን የኋይትሀውስ ምርጫዎችን በማሸነፍ በታሪክ ሁለተኛው ፕሬዚዳንትም ሆነዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
