በክልሉ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት እና እምቅ አቅም ለመጠቀም የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ችሎታን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ

Spread the love

የክልሉ ኢኖቬሽን እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ከቦንጋ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፎች ማስፈፀሚያ ላይ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በቦንጋ እየተሰጠ ይገኛል።

የቦንጋ ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ምክትል ኘሬዚዳንት ዶክተር ከለለው አዲሱ ባስተላለፉት መልዕክት ዓለም የደረሰበት የቴክኖሎጂ አቅም ደረጃ ጋር እኩል መራመድ የህሊውና ጉዳይ በመሆኑ እኩል ተወዳዳሪ ለመሆን የቴክኖሎጂ ስትራቴጂ ነድፎ በቁርጠኝነት ማስፈፀም ይገባል ብለዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ የወሰዱት ቁርጠኛ እርምጃ በአፍሪካ ፈር ቀዳጅ መሆኑና በዚህም በሀገራችን በባለፉት ዓመታት በርካታ ኢኒሼቲቮች ተቀርፀው ሲተገበሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግና ራዕይዋን ለማሳካት የዘርፉ ፖሊሲና የህግ ማዕቀፎች ዋነኛ መሳሪያ መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ: የሀገራችንን ብልፅግና ለማረጋገጥ እተሰራ ያለው የድጅታል አካታችነት ስራ ላይ ዩኒቨርስቲው የሚጠበቅበትን ድርሻ እንደሚወጣም ተናግረዋል።

የክልሉ ኢኖቬሽን እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘመድኩን ሰለሞን ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ክልሉ በተፈጥሮ ሀብት እና እምቅ አቅም የታደለ በመሆኑ ይህንን አቅም ለመጠቀም የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ችሎታን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ መድረክ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እና ህጎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መዘጋጀቱ በዘርፉ ግንዛቤ ከማግኘት ባለፈ ልምድ ለመለወጥ የሚረዳ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

ሀገራችን በቴክኖሎጂው ዘርፍ ልማት ላይ የሰጠችውን ትኩረትና ያስቀመጠቻቸውን ኢላማዎች ከፖሊሲውና ከህግ ማዕቀፎቿ በመረዳት የተፈጠረውን መልካም እድል ወደ ውጤት መቀየር ይገባል ያሉት ሃላፊው የሚፈለገው የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ ለመድረስ ፖሊሲና የህግ ማዕቀፎችን ተገንዝቦ መተግበር እንደሚገባም አሳስበዋል።

በአሁኑ ሰዓት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የፖሊሲና ስትራቴጂ፣ ጥናትና ምርምር አናሊስት ዶ/ር አበበ ሞላ ለስልጠናው የተዘጋጀ ሰነድ እየቀረበ ይገኛል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *