በክልሉ የተጎዱ መሬቶችን የማገገምና የአካባቢ ጥበቃ ስራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መኾኑ ተገለፀ።

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሸካ ዞን የኪ ወረዳ በአርሶ አደር መር የተፈጥሮ ሀብት ማገገሚያ ፕሮጀክት አማካኝነት የተጎዱ መሬቶችን የመንከባከብ እና የችግኝ ተከላ ተካሂዷል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የአነስተኛ መስኖ ዳይሬክተር አቶ አሚኖ መሐመድ እንደገለጹት፤ የዚህ ንቅናቄ ዋና ዓላማ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ በደን በመሸፈን የአፈር ለምነትን ማሳደግና የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማረጋገጥ ነው።

ፕሮጀክቱ አርሶ አደሩ አካባቢውን እየጠበቀ በተጓዳኝ በኑሮ ማሻሻያ መርሃ ግብሮች ተጠቃሚ የሚሆንበትን ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ ከመደበኛው የችግኝ ተከላ የተለየ ያደርገዋል።

በሌላ በኩል በዞኑ በ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ቡናን ጨምሮ ከ23 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም የ10 በመቶውን የበልግ ተከላ እቅድ ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ ስንታየሁ ጌታሁን ጠቁመዋል።

በበቆ ቀበሌ የተካሄደውን የደን ተከላ መርሃ-ግብር በነቂስ በመውጣት የተሳተፉት የአካባቢው ነዋሪዎችም፤ የተጀመረው የተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ለኑሮአቸው መሻሻል ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ለማሳደግ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *