ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሸጋገር የሚደረገውን ጉዞ ማፋጠን ይጠበቅብናል፦ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በብልፅግና ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤት የቀረቡ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ጋር በቀጣይ ተልዕኮዎች ዙሪያ ክልላዊ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ 7ኛውን ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ በስኬት በማጠናቀቅ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሸጋገር የሚደረገውን ጉዞ ማፋጠን ይጠበቅብናል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በመንግሥትና በፓርቲ መሪነት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ልማት እንዲሁም በሰላምና ፀጥታ ዘርፎች የተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገባቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል።

ፓርቲው ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የኑሮ ውድነት፣ የትራፊክ ፍሰት፣ የነዳጅ አገልግሎት፣ የሕገ-ወጥ መሣሪያ ዝውውር እና የኮንትሮባንድ ንግድ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ ያለውን ሥራ የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ፓርቲው በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለህዝቡ የገባውን ቃል ሕዝቡን በማሳተፍ ደረጃ በደረጃ ጥያቄዎችን በማዳመጥ እየፈታ መቆየቱንም አስረድተዋል።

አሁንም ፓርቲው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫን በድል በማጠናቀቅ የተጀመረውን የለውጡ ጉዞ ለማስቀጠል በሚያደርገው ርብርብ የሕዝቡ ተሳትፎ እንዲጠናከርም ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ጠይቀዋል።

የዛሬው መድረክ ባለፉት ዓመታት የነበሩ ጥንካሬዎችንና ድክመቶችን በመለየት፣ በቀጣይ ለሕዝብ የተገባውን ቃል በተሻለ አቅም ለመፈጸም የጋራ ግንዛቤ የሚፈጥር መድረክ መሆኑንም ኢንጂነር ነጋሽ ገልጸዋል።

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን እንደተናገሩት፤ ፓርቲው ባለፉት ዓመታት አገራዊ ተልዕኮዎችን በመፈጸም፣ የለውጥ ሥራዎችን በማጽናትና የአገር ልማትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ጥረቶችን አድርጓል።

በዚህ ሂደት በርካታ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙም፣ የተጀመሩ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራዎችን በማጠናከር አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

አቶ ፍቅሬ አማን አክለውም፤ ፓርቲው በለውጡ ማግስት ያካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ በሂደቱና በውጤቱ ዴሞክራሲያዊ መሆኑ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አገራት ተምሳሌታዊ ምርጫ ማካሄድ መቻሏን ያሳየ ነበር ብለዋል።

በተለይም የዘመናት የሕዝብ ጥያቄ የነበረው በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እንደ 11ኛ ክልል መመስረቱን አስታውሰዋል።

ከክልሉ ምስረታ በኋላም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፎች ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውንና የሕዝቡ ተጠቃሚነት መረጋገጡን ጠቅሰዋል።

በክልሉ የዘንድሮ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በየደረጃው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፣ የቅስቀሳ ሥራዎችም እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በዚህ ከዕጩዎች ጋር በቀጣይ ተልዕኮ ዙሪያ በሚደረገው የምክክር መድረክ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በልማትና በመልካም አስተዳደር የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *