



አስተዳዳሪዎቹ ተረጂነትና ልመናን ለማስቀረት ችግሮችን በራስ አቅም የመሸፈን አቅም እየተፈጠረ ይገኛልም ብለዋል ፡፡
ተረጂነትና ልመና እንደ ሀገር መለመድ የለበትም ያሉት የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን አመራሩ ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት በራስ አቅም ችግሮችን ለመቅረፍ ምርትና ምርታመነትን ለማሳደግ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል ፡፡
በዚህም በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ የሚከሰተውን ችግር ለመቅረፍ እንዲያስችል በዞኑ ከተለየው 257 ሄክታር መሬት ውስጥ በበልጉ እርሻ ከ66 ሄክታር በላይ መሬት በሰብል መሸፈኑን ተናግረዋል ፡፡
በመኸር የግብርና እርሻ በሰብል ያልተሸፈኑ የወልና ያልለሙ ማሳዎችን ትኩረት በመስጠት በሰብል መሸፈን ስራ እንደሚሰራም አቶ ሀብታሙ ገልጸዋል ፡፡
በዞኑ ዝናብን ተከትሎ በሚከሰተው የመሬት መንሸራት ምክንያት ዜጎች እንዳይቸገሩ ከወዲሁ የአደጋ ስጋት የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት በውስጥ የሰፈራ ፕሮግራም ለማስፈር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል ፡፡
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ ተረጂነትንና ልመናን ለማስቀረት በራስ አቅም ችግሮችን ለመቅረፍ በሚደረገው ርብርብ በዞኑ ለዚሁ ተግባር 7 ሄክታር መሬት በሰብል መሸፈኑን አስረድተዋል ፡፡
በዞኑ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ እርሻ እንዲገቡ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ አበበ ተናግረዋል ፡፡
በመኸር የግብርና እርሻ ተረጂነትን እና ልመናን ለማስቀረት በማሽላና በሩዝ እንዲሁም በባቄላ ምርት ወጣቶችንና አርሶ አደሮችን በማደራጀት ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ አበበ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራዎችን በማጠናከር ለዚሁ ተግባር በተከፈተ የባንክ ሂሳብ ተቀማጭ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው እየተሰሩም ይገኛል ብለዋል ፡፡
አቶ ታከለ ተስፉ የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተረጂነትን ለማስቀረት ከተጀመረ ወዲህ እንደ ዞን ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡
ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ የተነሳ ረጂ ሀገራት ፊታቸውን ማዞር የጀመሩበት ወቅት በመሆኑ መንግስት ፈጥኖ ተረጂነትን በራስ አቅም ማስቀረት የሚቻልበትን ኢንሼቲቭ መንደፉ ተገቢነት ያለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
እንደ ኮንታ ዞን ከዝናብ መብዛት ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ በሚከሰተው የመሬት መንሸራተት ህብረተሰቡን ለችግር ተጋላጭ እያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል ፡፡
ችግሮችን ፈጥኖ ለማረምና ህብረተሰቡን ከችግር ለማውጣት ተረጂነትንና ልመናን ለማስቀረት በዞኑ ባለፉት ጥቂት ወራቶች የሚበረታታ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል ፡፡
የራስን ሰብዓዊ ወጪ በራስ አቅም መሸፈን ይገባል ያሉት አቶ ተስፉ በዞኑ ወቅታዊ ክስተቶችን መነሻ በማድረግ ትርፍ ምርት በማምረትና በማከማቻ መጋዘን እህል በማከማቸት ለሰብዓዊ እርዳታ ራስን ማዘጋጀት ይገባል በሚል ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል ፡፡
ባሳለፍነው የበልግ እርሻ ለዚሁ ዓላማ ብቻ 130 ሄክታር መሬት በሰብል መሸፈኑን በመግለጽ 1400 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ እንደሚገንም ገልጸዋል ፡፡
በመኸር የግብርና እርሻ ወቅት ከ300 በላይ ሄክታር ማሳ በተለያዩ ሰብሎች ለዚሁ ዓላማ እንደሚለማም አቶ ታከለ ተስፉ ተናግረዋል ፡፡
በገንዘብ ደረጃ ለዚሁ ዓላማ ሊውል የሚችል ከ2 ሚሊዮን በላይ ብር በተከፈተ የባንክ ሂሳብ ተቀማጭ መደረጉንም ገልጸዋል ፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእርሻና ሆልቲካልቸር ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ በበኩላቸው ተረጂነትና ልመና የሀገርን ሉዓላዊነት ከብር ዝቅ የሚያደርግ ተግባር በመሆኑ ይህን ለማስቀረት እንደ ሀገር በራስ አቅም ችግሮችን የመፍታት ኢኒሼቲቭ ከተጀመረ በአንድ ዓመት ውስጥ በክልሉ የሚበረታቱ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል ፡፡
በክልሉ በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከባለፈው መኸር፣ መስኖና በልግ ወቅት የግብርና ስራዎች ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ትኩረት በመስጠት እየተሰራም ይገኛል ብለዋል ፡፡
በዚህ መኸር 70 ከመቶ በክልሉ አቅም የሚመረትና 30 ከመቶ ከፌ9ዴራል መንግስት በሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚሰራ መሆኑን አቶ አሸናፊ ተናግረዋል ፡፡
በዚህም ከ1200 በላይ ሄክታር መሬት በአዝዕርት ሰብሎችና ከ170 በላይ ሄክታር መሬት በሆልቲካልቸር ሰብሎች በማልማት ከ66 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት በመኸር እርሻ ለማምረት የመነሻ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል ፡፡
በክልሉ በተፈጥሮ አደጋ የሚከሰቱ ችግሮችን በራስ አቅም ለመቅረፍ እንዲያስችል አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሚገኝ አቶ አሸናፊ ተናግረዋል ፡፡
በታጠቅ አበበ
