ረቂቅ በጀቱ 1.93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ መቅረቡ የዋጋ ንረት እንዳይባባስ እና የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲኖር ያግዛል – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

Spread the love

የፌደራል መንግስት በ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 1.93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ ቀርቧል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ረቂቅ በጀቱ 1.93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ መቅረቡ የዋጋ ንረት እንዳይባባስ እና የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲኖር ያግዛል ብለዋል።

“ባለፉት ዓመታት አጠቃላይ የበጀት አጠቃቀማችን እና የገቢ አሰባሰብ አቅማችን በጣም እየጨመረ መቷል” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በተለይም ባለፉት 7 ዓመታት 3 እና 4 እጥፍ ሀገሪቱ ማደጓንም ነው ያነሱት።

የፌደራል መንግስት በ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 1.93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ መቅረቡ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ያገናዘበ ስለመሆኑም ነው የጠቀሱት።

የበጀት ሁኔታ ሲታይ ገቢ እና ወጪ ተጠንቶ እንደሆነ የሚናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የዘንድሮ የበጀት ዝግጅት ውስጥ 1.5 ትሪሊዮን የሚሆነው የሀገር ውስጥ ገቢ እና የውጭ እርዳታ ያካተተ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የፌደራል መንግስት በ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀቱ በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን የሚደጉም ስለመሆኑም አንስተዋል።

በጀቱም መሰረተ ልማቶች ፣ትምህርት ፣ ግብርና ፣ ጤና ላይ መሰል ጉዳዮች ላይ እንደሚውልም ጠቁመው፤ ከዚህ ባለፈ በክልሎች ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት እንዳለም ነው ያነሱት ። አጠቃላይ የበጀቱ ትኩረት ደሀ ተኮር እና ልማት ላይ መሆኑንም አስምረውበታል።

በሀገሪቷ ላይ በርካታ ስኬቶች ስለመኖራቸውም አንስተው፤ “ለመጀመሪያ ጊዜ ከብሔራዊ ባንክ ምንም ብር ሳንበደር የበጀት ዓመቱ ሊገባደድ ነው” ብለዋል።

የዋጋ ንረት እየቀነሰ መቷልም ብለው፤ በተለይም የዋጋ ንረት ዜጎች ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስም እየተሰራ እንደሆነ ሚኒስቴር ዴኤታው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ረቂቅ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ውይይት ተደርጎበት ለዝርዝር እይታ ለቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *