




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ዘርፍ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ከዞን እና ከተማ አስተዳደር ከትምህርት እና ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ መዋቅሮች ጋር በሁለትዮሽ “ቅንጅታዊ ሥራዎችን በማጠናከር የድርሻችንን እንወጣ” በሚል መሪ ቃል በ2016 አፈፃፀምና በ2017 ዕቅድ ላይ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ አካህዷል፡፡
በሁለትዮሽ ምክክር መድረክ ላይ የተሳተፉ አካላት በበኩላቸው የወሳኝ ኩነት ተግበራትን ውጤታማ ለማድረግ የሚታዩ ችግሮቹን ማስተካከልና የመረጃ ስርዓቱን ለማዘመን ታብሌት ምዝገባ ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ስራው በቅንጅት እየተሰራ እንዳለ አንስተው የተሰሩ ስራዎችን የሪፖርቱ አካል ከማድረግ የሚታዩ ጉድላቶችን በጋራ መፍታት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ተወካይ እና የክልሉ ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አለሙ፤ የወሳኝ ኩነት ለትምህርት ስራውም፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚው እና በማህበራዊ ሂደት በጣም ወሳኝ ተግባር መሆኑ ገልጸው በጋራ ተቀናጅተው መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
በትምህርቱ ዘርፍ ያለው አመራር በተቀናጀ መልኩ በመስራት የምዝገባ ስርዓቱን ውጤታማ ማድረግ የሚታዩ ጉድላቶችን ማረም እንደሚጠበቅ አቶ ሀብታሙ አሳስበዋል ፡፡
የክልሉ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ደነቀ እንደተናገሩት የትምህርት ተቋማት ቀጣይነት ያለው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ግንዛቤ ዙሪያ ተማሪዎች የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግና በቀጣይም ቅንጅታዊ ተግባርን ማጠንከር እንደለበት ገልፀዋል ፡፡
ለዚህም የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓትን ከመሠረታዊ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካታት ማስቻል እንደሚያስፈልግ ነው አቶ ሰለሞን የገለጹት፡፡
ለወሳኝ ኩነት ምዝገባ መሳለጥ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የማይተካ ሚና እንዳለዉ ጠቁመው ለተግባራዊነቱ ስኬት የሚደረጉት ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ደስታ ገናሜ በበኩላቸው የልደት ሰርተፍኬት መሠረት በማድረግ የተማሪዎች ምዝገባ ማካሄድ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ትምህርት ቤቶች መረጀ ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ የተማሪዎች ምዝገባ እንዲኖር ሰፊ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል፡፡
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ስለወሳኝ ኩነት ጠቀሜታ ተገቢ የሆነ የግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡
በተከተል ወ/ሚካኤል
